አውስትራሊያ የኮረናቫይረስ ክትባት ፕሮግራሟን በወርኃ ፌብሪዋሪ አጋማሽ ላይ ለመጀመር መሰናዶዋን እያከናወነች ነው፡፡
25 ሚሊየን ሕዝብ ያላት አውስትራሊያ እስካሁን 114.8 ሚሊየን ክትባቶችን ከሶስት የተለያዩ ምንጮች Oxford/AstraZeneca, Novavax እና Pfizer/BioNTech ሸምታለች።
ተጨማሪ ክትባቶችም ከCOVAX እንደሚገኝ የጤና ዲፓርትመንት አስታውቋል፡፡የአውስትራሊይ መንግሥት የፓስፊክና ምሥራቅ እስያ ጎረቤት አገራት ሰዎች የቫይረሱ መከላከያ ክትባቶችን በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት እንዲያገኙ ግማሽ ቢሊየን ዶላርስ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡
ቫይረስ ዓጤድ
የዓለም ጤና ድርጅት (ዓጤድ) ለደኃ አገራት ከሚቀጥለው ወርሃ ፌብሪዋሪ ጀምሮ ከፋይዘር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት 40 ሚሊየን ክትባቶችን ይሰጣል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቫክስን ፕሮግራም ተከትሎ በመቶ ሚሊየን የሚቆጠሩ ክትባቶችን ለደኃና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ያዳርሳል፡፡
ለክትባት ስርጭቱ እስካሁን ይሁንታን ያገኘው የፋይዘር-ባዮእኤንድቴክ ክትባትን ብቻ ነው፡፡
የዓጤድ ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም ስለ ጅምሩ አበራትችነት ሲናገሩ " የኮቫክስ በፌብሪዋሪ ክትባቶችን የማዳረስ ጅማሮ አበረታች ነው፡፡ ኮቫክስ በዓመቱ መጨረሻ ሁለት ቢሊየን ክትባቶችን ለማዳረስ በመሰናዶ ላይ ነው" ብለዋል፡፡
የዑጋንዳ ጦር
በሶማሊያ የሚገኘው የዑጋንዳ ሰላም አስከባሪ ጦር ከ180 በላይ ከአልቃይዳ ጋር ንኪኪ ያላቸውን ተዋጊዎች ደምስሷል። ታጣቂዎቹ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ካምፖች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዕቅድ እንደነበራቸው ተነግሯል፡፡
የዑጋንዳ ሕዝብ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ከመዲናይቱ ሞቃዲሾ 100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በምትገኘው የአልሻባብ መሸሸጊያ ላይ ባደረሱት ጥቃት ታጣቂዎችን ከመደምሰሳቸውም ባሻገር ወታደራዊ መሣሪያዎችንና ትጥቆችን አጋይተዋል፡፡
የዑጋንዳ ጦር ሶማሊያ ያለው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሓይል አካል በመሆን የአልሻባብ አሸባሪ ቡድንን በመክላት ለማዕከላዊ መንግሥት ድጋፍ ለመቸር ነው፡፡
አልሻባብ በ2011 በአፍሪካ ኅብረት ወታደሮች በደረሱበት ጥቃቶች ተቆጣጥሯቸው የነበሩትን በርካታ ሥፍራዎች እንዲለቅ የተደረገ ቢሆንም አሁንም ድረስ የጠብመንጃና ቦምብ ጥቃቶችን እያደረሰ ነው፡፡
ተቃውሞ በራሽያ
ራሽያ ውስጥ በተካሄደ አገር አቀፍ ተቃውሞ ሳቢያ ከ2000 በላይ ሰልፈኞች ለእሥር ተዳርገዋል፡፡
በተለያዩ ከተሞች በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሠልፈኞች የተመሙ ሲሆን፤ ለተቃውሞ ሠልፈኞቹ ዘብጥያ መውረድ አስባብ የሆነው የተቃዋሚ ቡድን መሪ አሌክሲ ናቫልኒ እሥራትን ተቃውመው አደባባይ መውጣት ነው፡፡
ለእሥራት ከተዳረጉት ውስጥ የአቶ ናቫልኒ ሚስት ዮሊያ ናቫልናያ ይገኙበታል፡፡
የተቃዋሚ ቡድ መሪው ባለፈው ሳምንት ጃኑዋሪ 17 እሥር ቤት የተከተቱት በሕይወታቸው ላይ ከተቃጣ የመርዝ ጥቃት በአገረ ጀርመን አገግመው ወደ ሞስኮ እንደተመለሱ ነው፡፡
አቶ ናቫልኒ ለተቃጣባቸው የመርዝ ጥቃት የክሬምሊን እጅ እንዳለበት ሲገልጡ፤ በክሬምሊን በኩል ሐሰት የሚል ማስተባበያ ተሰጥቷል፡፡
የተቃውሞ ቡድን አባላት ራሽያ ለውጥ ያስፈልጋታል ባይ ናቸው።

