የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሐምሌ 16 በፀጥታ መድፍረስ ሳቢያ በጋምቤላ ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ከፍተኛ ጉዳትና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ መንግሥት የሁነቱን አሳሳቢነት ተገንዝቦ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል።
ኮሚሽኑ ባካሔደው ምርመራ መሠረት በተለይም ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ላለው የጸጥታ ችግር መነሻ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ በተወሰኑ ነዋሪዎች መካከል የተነሳ አለመግባባት መሆኑን ማወቅ እንደቻለ ገልጧል።
አይያዞም፤ አለመግባባቱን ተከትሎ የተለያየ ብሔር ታጠቂ ቡድኖች በኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግ ወረዳ፣ በጋምቤላ ከተማ ብሔር ብሔረሰቦች ተብሎ በሚጠራው አካባቢና በከተማው በሚገኙ ሌሎች ሠፈሮች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን፤ በሳቢያውም የበርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ግድያ መፀሙን፣ ለአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና ንብረት ውድመት መዳረጋቸውንም አስታውቋል።
ጉዳዩን አስመልክቶንም የክልሉን የጸጥታና የአስተዳደር ኃላፊዎችን በማነጋገር ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል።
በተጨማሪም የፌዴራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተውጣጣ ኃይል ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተጨማሪ ተሰማርቷል። ይህም የክልሉን ጸጥታ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ያረጋጋው ሲሆን፣ በጋምቤላ ከተማ ተቋርጦ የነበረው መደበኛ እንቅስቃሴ እንዲጀመር አስችሏል።
" በክልሉ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ አፈጻጸም ነዋሪዎችን ለተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይዳርግ መከላከልን ጨምሮ፣ በክልሉ በተለያየ ወቅት የሚያገረሹ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ጉዳት የዳረጉ ጥቃቶችን እና ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም ተጨማሪ ትኩረት እና ክትትል ማድረግ ይገባል" ሲልም ኮሚሽኑ በመግለጫው አፅንዖት ሰጥቶ አሳስቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህንኑ ተግባር ለመደገፍ እና በተለይም በነዋሪዎች እና በክልሉ በተጠለሉ ስደተኛ ካምፖች ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ከነዋሪዎች፣ ከስደተኞች ተወካዮች፣ ከተቀባይ ማኀበረሰብ ተወካዮች፣ ከፌዴራል እና ጋምቤላ ክልል ጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም በስደተኞች አያያዝ ላይ ከሚሠሩ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የተውጣጣ ጊዜያዊ አስተባባሪ የሥራ ቡድን ማዋቀር ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚኖረው” መሆኑን ገልጸው፣ ኢሰመኮ በማድረግ ላይ የሚገኘው ክትትል የሚቀጥል ነው ብለዋል።