የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረማርያም በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን መጋቢት 14, 2014 ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ለዋና ሥራ አስፈፃሚው ስንብት አስባብ የሆነውም "የጤና እክል" እንደሆነና አቶ ተወልደ ላለፉት ስድስት ወራት ሕክምናቸውን በዩናይትድ ስቴትስ መከታተላቸውን ገልጧል።
አቶ ተወልደ ይህንኑ ምክንያት አድርገው በሥራ ኃላፊነታቸው ላይ መቀጠል እንደሚያውካቸው በመግለጽ ለአየር መንገዱ ቦርድ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውንና የሥራ መልቀቂያ ጥያቄያቸውም በቦርዱ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘቱን መግለጫው ጠቅሷል።
በምትካቸውም ቦርዱ አዲስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደሚተካ ተነግሯል።
እ.አ.አ በ2011 በአቶ ግርማ ዋቄ እግር ተተክተው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው የተመደቡት አቶ ተወልደ ባለፈው አንድ አሠርት ዓመት የአየር መንገዱ ዓመታዊ ገቢው ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ተነስቶ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ከፍ እንዲል፣ የአውሮፕላኖች ቁጥር ከ33 ወደ 130 እንዲያድጉ፣ የመንገደኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሚነት ከ3 ሚሊየን ወደ 12 ሚሊየን እመርታ እንዲያስገኝ ማስቻላቸውንና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ የስኬት አስተዋፅዖዎቻቸው በአየር መንገዱ መግለጫ ተመልክተዋል።
አየር መንገዱ ለአስተዋፅዖዎቻቸው ምሥጋናውን አቅርቧል፤ መልካም ጤናም ተመኝቷል።
አቶ ተወልደ በ2011 ዋና የሥራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ከመመደባቸው በፊት በ1985 የትራንስፖርት ወኪል በመሆን ሥራቸውን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀመሩ ሲሆን፣ በጭነት አገልግሎት፣ የሽያጭና ግብይት ዘርፎችን አካትቶ በተለያዩ ገዲብ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ተሰማርተው ሠርተዋል።
በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ኃላፊነት በነበሩበት ወቅት "የአፍሪካ የዓመቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ" ሽልማትን ጨምሮ በርካታ አኅጉራዊ ሽልማቶችን ተሸልመዋል።
አቶ ተወልደ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በምጣኔ ሃብት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ሁለተኛ ዲግዲያቸውን ከእንግሊዝ Open University በንግድ አስተዳደር አግኝተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ እ.አ.አ ከ2004 እስከ 2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ያገለገሉት አቶ ግርማ ዋቄ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።

ዩክሬይን ክሬምሊን
የፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅና የሩስያ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ልዩ ልዑክ የነበሩት አናቶሊ ቹባይዝ በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ የሥራ ኃላፊነታቸው ለቀቁ።
የልዩ ልዑኩን ከሥራ ኃላፊነት መልቀቅና ላይመለሱ ሩስያን ለቅቀው መውጣትን ክሬምሊን ለሮይተርስ አረጋግጧል።
አቶ ቹባይዝ በልዩ ልዑክነት ከመሾማቸው በፊት በርካታ የንግድና የፖለቲካ ቁልፍ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው የሠሩ ሲሆን፤ በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ ኃላፊነታቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁ የመጀመሪያው የሩስያ ባለስልጣን ናቸው።
ማድሊን ኦልብራይት
የዩናይትድ ስቴትስ የመጀመሪያዋ የሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማድሊን ኦልብራይት በ84 ዓመታቸው በካንሰር ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ቼኮዝሎቫኪያ የተወለዱትና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከናዚ ጥቃት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡት ኦልብራይት በፕሬዚደንት ክሊንተን ከ1977 እስከ 2001 በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ተሹመው ሠርተዋል።

ማድሊን ኦልብራይት ቀደም ሲልም በ1990ዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴት ስ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

