ቫይረስ ኢድ
በዛሬው ዕለት እሑድ ሜይ 24 የኢድ አል ፈጥር በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የኮቪድ - 19 ገደቦች ተጥለው ባሉበት ሁኔታ ነው።
የማኅበረሰብ መሪዎችም የእምነቱ ተከታዮች በየቤታቸው እንዲጸልዩ እያሳሰቡ ነው።
በተለምዶ የኢድ አል ፈጥር በዓል ማለዳ ላይ ሙስሊሞች በቤተ መስጊድ በታደሙበት በመላ አውስትራሊያ በጸሎት ይከበር የነበረ ቢሆንም፤ ዘንድሮ የአውስትራሊያ ብሔራዊ ኢማሞች ጉባኤ የኢድ ጸሎት በየቤቱ እንዲከናወን ወስኗል።
እንደ ቤተ መስጊዱ ሁሉ በተጣሉ ማኅበራዊ ገደቦች አስባብ የአውስትራሊያ ሙስሊሞች እንደ አምናና ካቻምናው ለሸመታ ገበያዎችን አላጨናነቁም።
ገበያዎችም ቀዝቅዘው ከርመዋል።

በሌላ በኩል ግና ባሕር ማዶ ቦዝኒያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ገደቦች ተጥለው ባሉበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያሸበረቁ የፊት ጭምብሎችን አጥልቀው ለምግብ ሸመታ ወደ ገበያ አዳራሾች ነጉደዋል።
አፍጋኒስታን ኢድ
የአፍጋን መንግሥትና ታሊባን ኢድ አል ፈጥርን አስመልክተው ለሶስት ቀናት የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በቅርብ ጊዜያት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተስፋፍቶ ሳለ ውጊያዎች ተፋፍመው ቀጥለው ነበር።
ይሁንና በወርኃ ረመዳን ማብቂያ ላይ ታሊባን የተኩስ አቁም ሲያውጅ የአፍጋን መንግሥትም በፊናው የተኩስ አቁም አዟል።
ባለፈው ወር ታሊባን ሙሉ የረመዳን ጾም ወርን ተኩስ እንዲያቆም ከአፍጋን መንግሥት ጥሪ ቢቀርብለትም አሌ ብሎ ነበር።
በወርኃ ረመዳን ውስጥም ታሊባን 146 ሰዎችን መግደሉንና 430 ማቁሰሉን የአፍጋን መንግሥት አስታውቋል።
ምርጫ ኢደን - ሞናሮ
ፊዮና ኮትቮይስ ለኢደን - ሞናሮ የሊብራል ፓርቲ የፌዴራል ምርጫ ሟሟያ ዕጩ ሆነው ተመረጡ።
የቀድሞዋ መምህርት፣ ሳይንቲስትና የአነስተኛ ንግድ ባለቤት፤ በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ የዕጩነቱን ውድድር አሸንፈዋል።

ዶ/ር ኮትቮይስ በቀድሞው የሌበር ምክር ቤት አባል ዶ/ር ማይክ ኬሊ ተይዞ የነበረውን የምክር ቤት ወንበር ለማሸነፍ የሚወዳደሩት የሌበር ዕጩ ከሆኑት ከንቲባ ክርስቲ ማክቤይን ጋር ነው።
የሟሟያ ምርጫው በወርኃ ጁን መጨረሻ ወይም ጁላይ መጀመሪያ ግድም ይከናወናል።

