የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ተጨማሪ ማዕቀቦችን ሩሲያ ላይ ጣሉ።
አዲሱ የባይደን ማዕቀቦች ያነጣጠሩት በቴክኖሎጂና ፋይናንስ ዘርፍ ነው። አቶ ባይደን ማዕቀቦቹ የሩስያን "የሕዋ ኢንዱስትሪ ያዳክማል፤ በዶላር፣ ዩሮ፣ ፓውንድና የን የመገበያየት አቅም ይቀንሳል" ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በሩስያ ባንኮችና ከፕሬዚደንት ፑቲን ጋር ባላቸው ብርቱ ትስስር ተጠቃሚ ናቸው ያለቻቸው ቱባ ከበርቴዎች ላይ ማዕቀቦችን የጣለች ቢሆንም ሩሲያ ከሉላዊ SWIFT የፋይናንስ ሥርዓት እስካልተከላች ድረስ ማዕቀቦች ብርቱ ጫና አያሳድሩም የሚል ትችት አግኝቷታል።
ሆኖም ሩሲያን ከሉላዊ SWIFT የፋናንስ ሥርዓት የማግለሉ ዕሳቤ አውሮፓ ላይ ሊያስከትለው የሚችላቸው መዘዞች አሳሳቢ በመሆናቸው በጀርመንና ጣሊያን ድጋፍ ሳያገኝ ቀርቷል።
አቶ ባይደን 7,000 የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ጦርን ለማጠንከር ወደ አውሮፓ እንደሚልኩ የገለጡ ሲሆን፤ ሆኖም ጦራቸው ለውጊያ ወደ ዩክሬይን እንደማይዘምት አስታውቀዋል።
ሩስያ ዩክሬይን ላይ ባካሔደችው የመጀመሪያ ቀን ጥቃት የ57 ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ተጠቅሷል፤ ይሁንና የጦርነቱ ሰለባዎች ቁጥር ከዚያም ከፍ ሊል ይችላል።
ቴኒስ
ኖቫክ ጆኮቪች የዓለም ቴኒስ አንደኛ ደረጃውን በሩሲያው ዳኒል ሜድቬዴቭ ሊነጠቅ ነው።
ለጆኮቪች የደረጃ መውረድ አስባብ የሆነው በዱባይ ቴኒስ ሻምፒዮን ሩብ ማጣሪያ ውድድር ወቅት በጂሪ ቬስሌይ ድል ተነስቶ ከውድድር ውጪ በመሆኑና የደረጃ ነጥቦቹ ዝቅ በማለቱ ነው።
ጆኮቪች በቬስሌይ የተረታው 6-4 7-6 (7-4) በሆነ ውጤት ነው።

