አውስትራሊያ የቻይናና የሰለሞን ደሴቶች የፀጥታ ረቂቅ ስምምነት እንዳሳሰባት ገለጠች

*** የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ ድጋፍ ሲባል ከሕወሓት ጋር ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታወቀ፤ ሕወሓት በበኩሉ ለሰላምና ሰብዓዊ ድጋፍ ዕድል ለመስጠት የግጭቱ መቆም ለስኬት እንዲበቃ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገለጠ።

Chinese President Xi Jinping meets with Solomon Islands' Prime Minister Manasseh Sogavare

Chinese President Xi Jinping meets with Solomon Islands' Prime Minister Manasseh Sogavare Source: Getty

የአውስትራሊያ ባለስልጣናት በቻይናና ሰለሞን ደሴቶች መካከል ለፊርማ ተቃርቦ ያለው አዲስ የፀጥታ ስምምነት ረቂቅ ያሳሰባቸው መሆኑን እየገለጡ ነው። 

ረቂቅ ስምምነቱ ላይ የሰለሞን ደሴቶች "ቻይና ፖሊስ፣ ባለ ትጥቅ ፖሊስ፣ የጦር ሠራዊትና ሌሎች የሕግ አስከባሪና ወታደራዊ ኃይሎችን" ወደ አገሪቱ እንዲዘልቁ ልትጠይቅ እንደምትችል ሠፍሯል። 

እንዲሁም፤ የቻይና መርከቦች ጉብኝት ሊያደርጉ፣ ተተኪ አቅርቦቶችን ሊያከናውኑና ሰለሞን ደሴቶች ላይ አጭር ቆይታን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቅሳል።

አውስትራሊያ ለሰለሞን ደሴቶች የረጅም ጊዜ የፀጥታ ጥበቃ እገዛዎችን የመስጠት ሚና ያላት ሲሆን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠልም ትፈልጋለች።

የአውስራሊያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ካረን አንድሩስ ከስምምነቱ ሂደት ጋር ተያያዥ የሆነው የቻይና በፓስፊክ አካባቢ መስፋፋትና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ "በአውስትራሊያ መንግሥት ዕይታ አሳሳቢ ነው" ሲሉ ገልጠዋል።  

ሰብዓዊ ድጋፍ - ትግራይ

የኢትዮጵያ መንግሥት መጋቢት 15 - 2014 ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዲሆን ግጭት ማቆሙን አስታወቀ።

መግለጫው የሰብዓዊ ድጋፉ ለዜጎች እንደምን ተደራሽ ሊሆን እንደሚችል ሲያብራራም "የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር እንዲሁም ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ የሚቀርብበትን ስርዓት የተሳለጠ እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የአለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የአለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማደረስ እንዲችሉ የአየር በረራ ተመቻችቷል።ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በአብአላ-መቀሌ የየብስ ትራንስፖርት መስመር በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መድረስ እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል" ብሏል። 

አያይዞም "ከተለመደው የተለዩ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግስት ይህ ውሳኔ ከወጣበት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ የመንግስት ጥረት እና ቁርጠኝነት የሰብዓዊ ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ የሚኖረው ስኬት የሚረጋገጠው በሌላኛው ወገን የሚገኘው አካል በተመሳሳይ ለዚህ አላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት ልክ መሆኑን መንግስት ያምናል" ሲል የሕወሓትን ስም ሳይጠቅስ የማሳሰቢያ ጥሪ አቅርቧል። 

 

ይህንኑ የመንግሥት መግለጫ ተከትሎ ሕወሓት በበኩሉ በተመሳሳይ ዕለት መጋቢት 15 - 2014 ባወጣው የአፀፋ መግለጫ፤ በተገቢው የጊዜ ሠንጠረዥ ውስጥ የትግራይ ሕዝብ የሚያሻውን ያህል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስገኙ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ "የግጭት ማቆሙ በአስቸኳይ ዕውን እንዲሆን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቁርጠኛ" መሆኑን አስታውቋል። 

 

አክሎም "ፖለቲካና ሰብዓዊ ሁኔታዎችን ማቆራኘት" ተቀባይነት እንደሌለው አሳስቦ፤ ሆኖም "የትግራይ ሕዝብና መንግሥት ለሰላም ዕድል ለመስጠት የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ" ብሏል። 

 

 

 


2 min read

Published

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now