ቪክቶርያ በኮሮናቫይረስ የተጠቁባት ሰዎች ቁጥር ወደ አምስት ከፍ በማለቱ ሜልበርን ላይ ገደቦችን ጥላለች።
ሆኖም ዛሬ ከቀትር በኋላ ተጨማሪ አራት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና በጠቅላላው ወደ ዘጠኝ ከፍ ማለቱን የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ አስታውቀዋል።
ከዛሬ ሜይ 25 ከምሽቱ 6:00pm ጀምሮ እስከ ጁን 4 ድረስ ጸንቶ በሚቆዩት ገደቦች መሠረት፤
- በየዕለቱ በመኖሪያ ቤት ውስጥ የመሰባሰብ መጠን በአምስት ሰዎች ተወስኗል
- በአደባባይ ከ30 ሰዎች መሰባሰብ አይቻልም
- በተለየ ሕመም ሳቢያ ካልሆነ በስተቀር የሥራ ቦታን ጨምሮ ዕድሜያቸ ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉ የፊት ጭምብሎችን ማጥለቅ ግድ ይላቸዋል
- ትምህርት ቤቶችና መሥሪያ ቤቶች ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ
- ከሜልበር ወደ ሪጂናል ቪክቶሪያ ሲጓዙ የገደቦቹን ደንብ መተግበር ይጠበቅብዎታል
- ከሪጂናል ቪክቶሪያ ወደ ሜልበርን ሲመጡ የገደቦቹን ድንጋጌ መፈጸም ግዴታ ይሆናል።
ቪክቶሪያ ውስጥ ዘጠኝ የሆቴል ወሸባ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ 14 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ይገኛሉ።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 14,892 ያህል የቪክቶሪያ ነዋሪዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ አካሂደዋል።
ኤምባሲ አፍጋኒስታን
ዓለም አቀፉ ጦር አፍጋኒስታንን ለቅቆ ለመውጣት በመሰናዶ ላይ ባለበት ወቅት አውስትራሊያ በሚመጡት ጥቂት ቀናት ውስጥ አፍጋኒስታን የሚገኘውን ኤምባሲዋን እንደምዘጋ አስታወቀች።
የኤምባሲውን መዘጋት ተከትሎም በሪጂኑ የሚገኙ የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳዮችና ንግድ ዲፓርትመንት ባለሥልጣናት የሥራ ጉብኝቶችን ያደርጋሉ።
የአውስትራሊያን የካቡል ኤምባሲ መዘጋት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ባወጡት መግለጫ እርምጃው "አውስትራሊያ ከአፍጋኒስታንና ሕዝቧ ጋር መቆሟን አይለውጥም" ብለዋል።

