ዛሬ እሑድ ኦክቶበር 25 ከረቡዕ ኦክቶበር 28 ጀምሮ የሜልበርን ከተማ ነዋሪዎች ላይ ተጥለው ያሉ ገደቦች መርገብ ይነገራል ተብሎ ተስፋ አድሮ የነበረ ቢሆንም በሜልበርን ሰሜናዊ ክፍለ ከተማ አዲስ በተከሰተ የኮሮናቫይረስ ሳቢያ ዕውን ሳይሆን ቀርቷል።
የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ስለ ውሳኔው መዘግየት ሲናገሩ "በዛሬው ዕለት የሜልበርን ከተማን አስመልክቶ በችርቻሮ፣ መስተንግዶና ሌሎች ጠቃሚ በሆኑ ዘርፎች ቀጣይ እርምጃዎችን ለማስታወቅ ተስፋ እንዳደርግነው አልሆነልንም"
"ዛሬ ያን ለማድረግ ያልበቃነውም 1000 ያህል በሰሜናዊ ክፍለ ከተማ የተከሰተው ቫይረስ ምርመራ ላቦራቶሪዎች ውስጥ ስለሚገኝ ነው። ውጤቶቹን ዛሬ እናገኛለን የተቀሩትንም በነገው ዕለት። ተጨማሪ ምርመራዎችም ቀኑን ሙሉ ይካሄዳሉ" ብለዋል።
አቶ አንድሩስ ይህ "የኋልዮሽ መመለስ" እንዳልሆነ ጠቅሰው ይልቁንም "ጥንቃቄ የተመላበት መገታት" እንደሆነ አሳስበዋል።
በማከልም - ዳታዎች ተሰባስበው መልካም ውጤቶች ከተገኙ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ውስጥ ሳይንሳዊ ዳታዎች ላይ ተመረኩዘው ውሳኔ ላይ በመድረስ የገደቦችን መላላት እንደሚያስታውቁ ገልጠዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ሜልበር ውስጥ 7 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲጠቁ አንድም ለሕልፈት የበቃ ሕይወት የለም።
የሜልበር የ14 ቀናት የቫይረሱ መስፋፋት መጠን ወደ 4.6 ያሽቆለቆለ ሲሆን ምንጫቸው ያልተለየ 9 ደርሷል።
የሪጂናል ቪክቶሪያ የ14 ቀናት የቫይረሱ መስፋፋት መጠን ወደ 0.2 ወርዷል።
ሪጂናል ቪክቶሪያ
አቶ አንድሩስ በዛሬው ዕለት ለሪጂናል ቪክቶሪያ ከ11:59pm ኦክቶበር 27 ጀምሮ በተጨማሪ የላሉ ገደቦችን አስታውቀዋል።
- የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ከ20 ሰው ባልበለጠ ለአንድ ሰው በ8 ስኩየር ሜትሮች
- ቤተ እምነቶች ከ20 ያልበለጡ ምዕመናንና በታካይነት አንድ የእምነት መሪን ጨምሮ በቤት ውስጥ መሰባሰብ
- ከቤት ውጪ ከ50 ያልበለጡ ምዕመናንና በታካይነት አንድ የእምነት መሪን ጨምሮ መታደም
- ከቤት ውጪ ከ50 ያልበለጡ ለቀስተኞች በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ይችላሉ
- አካል-ለአካል የማያነካኩ ስፖርቶች ዕድሚያቸው ከ18 በታች ለሆኑቱ በ1.5 ሜትር ርቀቶችን ጠብቀው መጫወት ተፈቅዶላቸዋል
- የቤት ውስጥ ዋና ከ20 ያልበለጡና ሁሉንም የዕድሜ ደረጃ አካትተው ክፍት ይሆናሉ
Share

