የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በዩክሬይን ላይ ጦርነት የመክፈቷ ኃላፊነት የሚያርፈው ዩክሬይንና የምዕራባውያን አገራት ላይ እንደሆነ ገለጡ።
ሩስያ የዩክሬይን ዘማች ጦሯን ለማጎልበት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ክተት ስትል፤ ከዩክሬይን የተነጠሉት ሉሃንስክ፣ ዶኔትስክ እና ዛፖሪዚህያ በፈቃዳቸው የሩስያ አካል ለመሆን የሕዝበ ውሳኔ ሂደት ላይ ናቸው።
በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተገኙት የሩስያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ሕዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ ምዕራባውያን የስሜት መታወክ እንደገባቸው አንስተው፤ ለሕዝበ ውሳኔው አስባቦቹም ዩክሬይንና ምዕራባውያን አገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዩክሬይን
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ለዩክሬይን እጃቸውን ለሚሰጡ የሩስያ ወታደሮች በርካታ የዋስትና ቃሎችን ገቡ።
ሩስያ ውስጥ ከ700 በላይ የጦርነት ተቃውሞ ሰልፈኞች ለእሥር መዳረጋቸውን የሰብዓዊ መብቶች ቡድናት አስታውቀዋል።
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ 300,000 ተጠባባቂ ወታደሮች ለውጊያ መሰማራት ያስቆጣቸው እንደሆነም ተገልጧል። ፕሬዚደንት ፑቲን የክተት ጥሪያቸውን እምቢኝ የሚል ማንኛውም ግለሰብ ብርቱ ቅጣት እንደሚያገኘው አስጠንቅቀዋል።
ፕሬዚደንት ዜለንስኪ በሩስያኛ ቋንቋ ባስተላለፉት የምሽት የቪዲዮ መልዕክታቸው የሩስያ ወታደሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
"ዩክሬይን ለእያንዳንዱ እጁን ለሚሰጥ ወታደር ሶስት ነገሮችን ዋስትና ትሰጣለች። አንድ፤ ሁሉንም ዓይነት የስምምነት ውሎች ተከትሎ ስልጣኔ በተመለበት መንገድ ትስተናገዳላችሁ። ሁለት፤ የእጅ አሰጣጣችሁን ሁኔታ ማንም ሰው እንዲያውቅ አይደረግም። ሩስያ ውስጥ ያለ ማንም ሰው እጃችሁን በፈቃደኝነት ስለመስጠታችሁ የሚያውቅ አይሆንም። ሶስተኛ፤ በእሥረኛ ልውውጥ ወደ ሩስያ ለመመለስ የሚያስፈራችሁ ከሆነ፤ ለዚያም መንገዶችን እንፈልጋለን። ዩክሬይን ድልን ለመቀዳጀት ማናቸውንም ነገሮች ታደርጋለች። እያንዳንዱ የሩስያ ዜጋ ይህን ሊረዳ ይገባል። አንዳችም የማታለያ ዘዴ ወራሪን አይረዳም። ቃሌን እሰጣችኋለሁ" ብለዋል።