ኒው ሳውዝ ዌይልስ በዛሬው ዕለት ከ109,545 የኮቪድ-19 ምርመራዎች ውስጥ 6,394 ሰዎች በቫይረሱ እንደተጠቁባትና ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረገ አለመኖሩን አስታወቀች።
በቫይረስ ተጠቅተው ትናንት ቅዳሜ ድረስ ሆስፒታል ውስጥ ይታከሙ በነበሩት 388 ሕሙማን ላይ በዛሬው ዕለት 70 ተጨማሪ በመሆን 458 ደርሰዋል።
በፅኑዕ ሕሙማን ክፍል ካሉ 52 ሕመምተኞች በስተቀር ተጨማሪ ሕመምተኛ አልታከለም።
***
ቪክቶሪያ
ቪክቶሪያ ከ72 ሺህ ምርመራዎች ውስጥ 1,608 ሰዎች በኮቪድ-19 እንደተያዙባትና የሁለት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስመዝግባለች።
ቪክቶሪያ ውስጥ በጠቅላላ በቫይረስ ተጠቅተው የነበሩ 17,600 ሰዎች ቁጥር ወደ 17,392 ዝቅ ብሏል።
374 ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ሲገኙ፤ 77 በፅኑዕ ሕሙማን 43 የአየር መተንፈሻ መሳሪያ ተገጥሞላቸው ይገኛሉ።
***
ደቡብ አውስትራሊያ
ደቡብ አውስትራሊያ በዛሬው ዕለት የ774 ነዋሪዎቿ በቫይረስ መጠቃትንና የኦሚክሮን ተዛማችነት መስፋፋትን ተከትሎ ከዕኩለ ለሊት ጀምሮ የሚፀና ገደቦች መጣሏን ፕሪሚየር ስቲቨን ማርሻል አስታወቁ።
በዚህም መሠረት፤ የአካል ማጠንከሪያ ሥፍራዎች ውስጥ በአንድ ሰው የሰባት ሜትሮች ርቀት፣ በቤት ውስጥ የመስተንግዶ ሥፍራዎች በአንድ ሰው አራት ሜትሮች፣ ከቤት ውጪ በአንድ ሰው የሁለት ሜትሮች ርቀት እንዲኖር ተደንግጓል።
17 ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ ሶስት በፅኑዕ ሕሙማን ክፍሎች የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።
***
ኩዊንስላንድ
ኩዊንስላንድ ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኮቪድ-19 ከተጠቁት ሰዎች ሶስት አራተኛዎቹ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች ነው።
ባለፉት 24 ሰዓታት 714 ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ ሰባት፤ ሰዎች ሆስፒታል ይገኛሉ። ለፅኑዕ ሕሙማን ክፍል የተዳረገ ታማሚ የለም።
***
ታዝማኒያ
ታዝማኒያ 44 ሰዎች በቫይረስ የተያዙባት ሲሆን፤ እስካሁን በቫይረስ የተጠቁ ነዋሪዎች ጠቅላላ ቁጥር 160 ደርሷል።
86 ሕሙማን የቤት ውስጥ ክብካቤ እያገኙ ነው።
***
ዛሬ ለቦክሲንግ ዴይ ሸመታ ገበያ የሚወጡ ሸማቾች ለቫይረስ ራሳቸውን እንዳያጋልጡ ባለስልጣናት እያሳሰቡ ነው።
በሌላ በኩል ግና ከፍተኛ ክብረ ወሰን የሚመዘገብበት የኦንላይን ግዢ በአማራጭነት እንደሚከናወን ይጠበቃል።
የፔይፓል አንድ አዲስ ጥናት እንደሚያሳየው ከ10 ሸማቾች ውስጥ አንድ ሸማች በዛሬ ዕለት ግዢ የሚፈፅመው ለገና በዓል ሊገዛ የሚሻውን በቅናሽ ለማግኘት እንደሆነ ጠቁሟል።
በየዓመቱ ዲሴምበር 26 የሚካሔደው የቦክሲንግ ዴይ ባህላዊ ሸመታ የመጨረሻው የበዓል ሰሞንና የዓመቱ ማጠቃለያ የግብይት ቀን ነው።

