ታሪን ብራምፊት ባለፈው አሠርት ዓመት ሰዎች ለአካላቸው ያላቸውን ምልከታና አተያይ ለመለወጥ ታትረዋል።
ትናንት ረቡዕ ጃኑዋሪ 25 / ጥር 16 በመዲናይቱ ካንብራ የዓመቱ አውስትራሊያዊት ሆነው ለአገር አቀፉ ዓመታዊ ሽልማት በቅተዋል።
ወ/ሮ ብራምፊት የአካል ገፀታ ንቅናቄ በ2016 የመሠረቱ ሲሆን፤ በዚያው ዓመትም "Embrace" በሚል መጠሪያ አካላዊ ገፅታ፣ ማኅበራዊ ሚዲያና ሴቶች ስለ ራሳቸው ያላቸውን ምልከታ ያካተተ ዘጋቢ ፊልም ቀርፀው አቅርበዋል።
ፊልሙ በ190 አገሮች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ቀልብ ለመሳብ በቅቷል። ይህንኑ ስኬት ተከትሎም በ2022 "Embrace Kids" ዘጋቢ ፊልም ለኧይታ አብቅተዋል።
ረቡዕ ምሽት ሽልማቱን በተቀበሉበት ወቅትም የአካልዊ ገፅታ ጉዳይ በተለይም በወጣቶች ዘንድ ልዩ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አሳስበዋል።
አክለውም "ለ70 ፐርሰንት አውስትራሊያውን ተማሪ ልጆች አካላዊ ገፅታ ቁጥር አንድ አሳሳቢ ጉዳያቸው ሆኗል" ብለዋል።
በሌላም በኩል፤ ፕሮፌሰር ቶም ካልማ የዓመቱ አረጋዊ አውስትራሊያዊ፣ አዌር ማቢሊ የዓመቱ ወጣት አውስትራሊያዊ፣ አማር ሲንግ የዓመቱ የአካባቢ ጀግና አውስትራሊያዊ ተብለው የአገር አቀፉ ዓመታዊ የክብር ሽልማት ተሸላሚዎች ሆነዋል።

በደቡብ ሱዳን ጦርነት ሳቢያ ለስደት ከተዳረጉት ቤተሰቦቹ ኬንያ ካኩማ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ በ1995 የተወለደውና ለአውስትራሊያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ሶኮሩስ ለመጫወት የበቃው አዌር ማቢል የዓመቱ ወጣት አውስትራሊያዊ ተሰኝቶ ተሸልሟል።
የሕይወቱን የመጀመሪያ 10 ዓመታት ኬንያ በስደተኝነት ያሳለፈው ማቢል አውስትራሊያ በዳግም ሠፈራ ፕሮግራም ከቤተሰቡ ጋር መጥቶ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተምሮ፤ በእግር ኳስ ጨዋታው ሂደት ጓደኞች ለማፍራትም በቅቷል።

ማቢል ለአደላይድ ዩናይትድ ክለብና በተለያዩ የዓለም አገራት ተዘዋውሮ እግር ኳስ ተጫውቷል፤ አውስትራሊያም ለ2022 የፊፋ ዓለም ዋንጫ ውድድር እንድታልፍ የድርሻውን ተወጥቷል።

