የኢትዮጵያን አገር አቀፍ ምርጫ 2013 አስመልክቶ የአውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጃፓን፣ ሉዘምበርግ፣ ኒውዚላንድ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ የኔዘርላንድስና እንግሊዝ ኤምባሲዎችና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ምርጫ ብቻውን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እንደማያስገኝ ወይም ተደቅነው ያሉ ተግዳሮቶችን እንደማይከላ በማንሳት ያለማወላወል ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማስገኘት የኢትዮጵያ መንግሥትንና ባለድርሻዎችን ያካተተ ትርጉም ያለው መጠነ ሰፊ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሔድ ጥሪ አቅርበዋል።
የጋራ ብልፅግናውና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮቹ አክለውም ብሔራዊ ውይይቱ "የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ዕድገት ለመከወን፣ የትግራይ ሁኔታን አካትቶ ፖለቲካዊ ዕልባት ለማበጀትና በመላ አገሪቱም ግጭትን ለመቀነስ" እንደሚረዳ አሳስበዋል።
ለዲሞክራሲያዊ ሂደቱ ስኬት እገዛቸውን እንደሚቸሩ ሲገልጡም "እንደ ረጅም ጊዜ ዓለም አቀፍ ሽርካነታችን፤ የኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ መስተዳድር ሽግግር እንደግፋለን" ብለዋል።
የምርጫውን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶም በምርጫ ምዝገባ ጠቃሚ የሆኑ መሻሻሎች መደረጋቸውን፣ የምርጫ ቦርድ ተዓማኒነት የመዳበር ሂደት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ኅብረተሰብና ሚዲያ ጋር ያሳያቸውን መስተጋብሮች በመልካም ጎኑ አንስተዋል።
በሌላ ጎኑም ምርጫው የተካሄደው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ታግተው ባሉበት፣ የሚዲያ ተወካዮች ትንኮሳ በገጠማቸው ሁነት፣ ፓርቲዎች በነፃነት የምርጫ ቅስቀሳዎችን ለማድረግ አዋኪ ሁኔታዎች ገጥሟቸው ባለበት ውስን ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ እንደሆነ አመላክተዋል። ለምክር ቤት አባልነት የተወዳደሩ ሴቶች ቁጥር ካለፉት አገር አቀፍ ምርጫዎች ጋር ሲነፃፀርም ሶስት እጅ ያህል ዝቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንኑ የጋራ ብልፅግናውና የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮቹን የጋራ መግለጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ወዳጅነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ሽርካዎች የምርጫውን ሂደት አስመልክቶ ያሳዩትን በጎ ፍላጎት አድንቋል። የምርጫ ቦርድ ተዓማኒነት የመዳበር ሂደት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ኅብረተሰብና ሚዲያ ጋር ያሳያቸውን መስተጋብሮች በመልካም ጎኑ ማንሳታቸውንም አወድሷል።
ሆኖም የምርጫውን ሂደት ዕውነታ አለመረዳት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ታግተው ባሉበት፣ የሚዲያ ተወካዮች ትንኮሳ በገጠማቸው ሁነት፣ ፓርቲዎች በነፃነት የምርጫ ቅስቀሳዎችን ለማድረግ አዋኪ ሁኔታዎች ገጥሟቸው ባለበት ውስን ፖለቲካዊ ምኅዳር ውስጥ ምርጫው እንደተካሄደ ተደርጎ መቅረቡ አሳሳች ገለጣ ነው ሲል በመፈረጅ ተቃውሟል። የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲካዊ አተያይን በማንጸባረቅ ሳቢያ አንድም ለእሥር ያበቃው ሰው እንደሌለ በመጥቀስም ተቃርኖውን አስታውቋል።
አያይዞም፤ 'በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያውያን የመረጡት ተወካዮቻቸውን ብቻ ሳይሆን ለሰላም፣ የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበርና የአገራቸውንም የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ያላቸውን የማይናወጥ አቋም ያሳዩበት ነው' ሲልም አተያዩን አመላክቷል።
በማጠቃለያውም ሽርካዎቻችን ያንን ውሳኔ እንደሚያከብሩና 'የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቸኛው የአገሩ ባለቤትና የዲሞክራሲ ጠባቂ እንደሆነ ሊረዱ ይገባል' ሲል ቋጭቷል።
ድንበር አልባ ሐኪሞች
የድንበር አልባ ሐኪሞች ቡድን ትናንት ጁን 25 ባወጣው ሐዘንና ውግዘትን ያዘለ መግለጫው ትግራይ ውስጥ የሶስት ባልደረቦች ግድያን አስመልክቶ "ሐዘናንችንን የምንገልጽበት ቃል የለንም። አሰቃቂ በሆነው ጥቃት ድንጋጤና ብስጭት አድሮብናል። የተሰማንን ጥልቅ ሐዘንም ለቤተሰቦቻቸውና ዘመድ አዝማዶቻቸው እንገልጣለን" ብሏል።
ሟቾቹም ማሪያ ሄርናንዴዝ - የድንገተኛ አደጋ አስተባባሪ፣ ዮሐንስ ሃለፎም ረዳ - ረዳት አስተባባሪና ቴድሮስ ገብረማሪያም ገብረሚካኤል - ሾፌር የነበሩ መሆናቸውን አስታውቋል። አስከሬናቸውም ከመኪናቸው ጥቂት ሜትሮች ርቆ መገኘቱንም ገልጧል።
ማሪያ ዕድሜዋ 35 ዜግነቷም ስፔንያዊት ስትሆን፤ ዮሐንስና ቴድሮስ ሁለቱም ዕድሜያቸው 31 እና ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ነበሩ።
የድንበር አልባ ሐኪሞች የሟች ባልደረቦችን አሟሟት ሁኔታ፣ ለግድያ ያበቃቸውን አስባቦችና ማን ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል አላመላከተም።

