የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ ኢትዮጵያን "ከውስጥና ከውጭ ኃይሎች ጥቃቶች የሚመክት ባሕር ኃይል እየተገነባ ነው" ሲሉ ገለጡ።
የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል በብቃትና በጥራት ለመገንባትም "የተማረ፣ የሰለጠነ፣ ዲሲፕሊን ያለውና አገሩን የሚወድ ቁርጠኛ የሆነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል" ብለዋል።
የባሕር ኃይል ዋና አዛዡ ይህን የተናገሩ ቢሾፍቱ በሚገኘው የባሕር ኃይል መሰረታዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተገኝተው ለሰልጣኖች ባደረጉት ንግግር ነው።
የኢትዮጵያ ኢምፔሪያል ባሕር ኃይል እ.አ.አ 1955 በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ሲሆን፤ እ.አ.አ ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በሚል ስያሜ እስከ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መነጠል ድረስ ቆይቷል።
የኢሕአዴግን ስልጣን መያዝና የኤርትራ ሉዐዓላዊ አገር መሆንን ተክትሎ የፈረሰው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል በእ.አ.አ 2018 የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር የኢትዮጵያን የፀጥታና የመከላከያ ኃይለ ለማጠናከር በወሰነው ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መልሶ ለመቋቋም በቅቷል።
የባሕር ኃይሉን መልሶ ለመገንባትም ኢትዮጵያ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር እ.አ.አ በ2019 ተዋውላለች።
የባሕር ኃይሉ የጦር ሠፈር ጂቡቲ ሲሆን፤ ዋና መሥሪያ ቤቱ ባሕር ዳር ነው።
የውጭ እርዳታ
የሌበር ፓርቲ ለቻይና ከሰለሞን ደሴቶች ጋር ከአዲስ የፀጥታ ስምምነት ላይ ለመድረስ መቅረብ የሊብራል/ናሽናልስ ቅንጅት መንግሥት የውጭ እርዳታ ቅነሳ አንዱ አስባብ ነው ሲል ተቸ።
አንድ ሾልኮ የወጣ ዶክሜንት እንዳመለከተው ስምምነቱ ምናልባትም ከአውስትራሊያ 2000 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ለቻይና ባሕር ኃይል የጦር ሠፈርን ሊያስገኝ እንደሚያስችል ጠቅሷል።
የሌበር ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ሂደቱን አስመልክቶ ሰኞ በብሔራዊ የፀጥታ ኤጄንሲዎች ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።
አቶ አልባኒዚ ሁነቱ በእጅጉ አሳሳቢ እንደሆነም ተናግረዋል።
ላይፍላይን አውስትራሊያ
ላይፍላይን አውስትራሊያ በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ይፋ በሚደረገው ዓመታዊ በጀት ተጨማሪ ድጎማ እንደሚያገኝ ተገለጠ።
ተጨማሪ ድጎማው በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ለቀውስ ድጋፍ አገልግሎት መስጫ የሚውል $52 ሚሊየን ዶላርስ ነው።
ድጎማው ላይፍላይን በሚቀጥለው ዓመት 176,000 የስልክ ጥሪዎችንና 4000 የአጭር ፅሑፍ መል ዕክቶች በቀን ውስጥ እንዲያስተናግድ እንደሚረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አስታውቀዋል።

