የማያንማር ፍርድ ቤት በጦር ኃይል ከስልጣናቸው ተገፍተው የወረዱትን አንግ ሳን ሱ ቺ ዛሬ ረቡዕ ኤፕሪል 27 በሙስና ተዘፍቀዋል በሚል የአምስት ዓመት እሥራት በየነባቸው።
በዚህ ዓመት ወርኃ ፌብሪዋሪ ላይ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከማያንማር መሪነታቸው የተገለሉት የኖቤል ሎሬዬት አንግ ሳን ሱ ሱቺ በርካታ የወንጀል ክሶች ተመስሮቶባቸዋል።
ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል $600,000 ዶላርስ በጥሬ ገንዘብና ወርቅ ጉቦ ተቀብለዋል፣ የምስጢራዊ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል፣ የምርጫ ማጭበርበር አካሂደዋል ተብለው ተወንጅለዋል።
ዛሬ ለአምስት ዓመታት ካስፈረደባቸው ክስ ባሻገር በሌሎች የተወንጀሉባቸው ክሶቹ ጥፋተኛ ከተባሉ እስከ 100 ዓመታት የሚያስፈርዱባቸው ይሆናሉ።
የ76 ዓመቷ የቀድሞዋ የማይንማር መሪ ቀደም ሲልም በጦር ኃይሉ ላይ አሳምፀዋል፣ የኮቪድ-19 ድንጋጌዎችና የቴሌኮሙኒኬሽን ሕግን ጥሰዋል በሚል የስድስት ዓመት የቤት ውስጥ እሥራት ተፈርዶባቸዋል።
በዛሬው ዕለት ብይን በተበየነባቸው ወቅት ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንዳያቀርቡ የታገዱ ሲሆን፤ የሱ ቺ ጠበቃዎችም ለብዙኃን መገናኛ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጡ ተከልክለዋል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ በተነሱ ብጥብጦች ከ1,700 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡና ከ13,000 በላይ ዘብጥያ እንደወረዱ የአካባቢው ዘገባዎች አመልክተዋል።

