የዋጋ ግሽበት በወርኃ ማርች ሩብ ዓመት ላይ ከተጠበቀው በላይ ንሮ 5.1 ፐርሰንት ደርሷል።
ይህም ካለፈው አንድ አሠርት ዓመት ወዲህ እንዲህ ባለ ፍጥነት ሲያሻቅብ የመጀመሪያው ሆኗል።
የዋጋ ግሽበቱ ወደ 5.1 ያሻቀበው ከዲሴምበር የሩብ ዓመት 2.1 ፐርሰንት ተንስቶ ነው።
ከ2010 ወዲህ ከብሔራዊ ባንክ ከ2 እስከ 3 ፐርሰንት የዋጋ ንረት ግምት በላይ ሲንርም ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።
የነዳጅና የኮንስትራክሽን ዋጋ ጭማሪ ለግሽበቱ ንረት በታካይ አስባብነት ተጠቃሽ ሆነዋል።
ይህንንም ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ቦርድ በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ሲታደም የወለድ መጠኑን አሁን ካለበት 0.1 ፐርሰንት ከፍ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ተገምቷል።
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የሩስያና ዩክሬይን ጦርነት አውስትራሊያን ጨምሮ በመላው ዓለም የኑሮ ውድነትን አባብሷል።
የነዳጅ፣ የምግብ ዘይት፣ የግሮሰሪና የእየር ቲኬቶች ዋጋቸው ፈጥኖ ካሻቀቡት ውስጥ ግንባር ቀደም ናቸው።

በቅርቡም በዚህ ዓመት መጨረሻ አውስትራሊያ ውስጥ የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ እስከ $7 ዶላርስ ሊደርስ እንደሚችል የአውስትራሊያ ካፌ ቤቶችና አስተናጋጆች ማኅበር ግምቱን አሳድሯል።

