በኒውዝላንድ - ክራይስትቸር መስጊድ ላይ የጠብመንጃ ጥቃት ፈጽሞ 51 ሰዎችን የገደለው አውስትራሊያዊ በሽብር ግድያ ተግባር ዕድሜ ይፍታህ ተበይኖበታል።
ዳኛ ካሜሮን ማንዴር በዛሬው ዕለት ብይናቸውን ሲያሳልፉ "አንተ አሸባሪ እንጂ ገዳይ አይደለህም… እስከምትሞት እስር ቤት ብትቆይም ያ ለፈጸምካቸው ወንጀሎችህ የቅጣት መስፈርቶችና ውግዘት በቂ አይሆንም" ብለዋል።

በጥቃቱ የቤተሰብ አባላታቸውን ካጡት ውስጥ አንዱ "እሱ ድል ተነስቷል። ከሰለባዎቹ ጋር ዓይን-ለዓይን ለመተያየት አልፈለገም። ጥላቻ በጸጥታ ተውጧል" በማለት ብይኑ ግድያውን በፈጸመው አውስትራሊያዊ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ተናግረዋል።
የውጭ ግንኙነት
የሞሪሰን መንግሥት የስቴትና ግዛት መንግሥታት ከውጭ አገራት የሚያደርጉትን ስምምነት ለመገደብ አቅዷል።
የፌዴራል ቅንጅት መንግሥቱ በዕቅዱ መሠረት በስቴት፣ ግዛት፣ የአካባቢ መንግሥታትና የሕዝብ ዩኒቨርሲቲዎች ከሌላ አገራት ጋር የተካሔዱትን ስምምነቶች ይከልሳል፤ ይሰርዛል።
ማናቸውም ከውጭ መንግሥታት ጋር የሚካሔዱ ስምምነቶች ዕውን እንዲሆኑ የፌዴራል መንግሥቱን ይሁንታ ማግኘት ግድ ይላል።
ቪክቶሪያ ከቻይና ጋር ያላት ሕጋዊ አስገዳጅነት አልባ የሆነ የ 'ሐር መንገድ' ስምምነት በፌዴራል መንግሥቱ ዘንድ የውጭ ተፅዕኖ ያሳድራል ተብሎ ሲታሰብ፤ በቪክቶሪያ መንግሥት በኩል ግና ስምምነቱ ከሥራና የንግድ መሠረተ ልማት ፕሮጄክትነት የዘለለ አይደለም ተብሏል።
የፌዴራል መንግሥቱ በሚቀጥለው ሳምንት ረቂቅ ድንጋጌውን ለፓርላማ የሚያቀርብ ሲሆን ድንጋጌውም ከዚህ ዓመት ማብቂያ በፊት በታችኛውና በላይኛው ምክር ቤቶች ፅድቅ እንዲቸርለት ይሻል።
ቫይረስ - ቪክቶሪያ
ቪክቶሪያ ውስጥ በዛሬው ዕለት 113 ሰዎች ኮቪድ -19 ተይዘዋል፤ የ23 ሰዎች ሕይወት አልፏል።
ሕይወታቸው ካለፉት ውስጥ 22ቱ የአረጋውያን መጦሪያ ነዋሪዎች ነበሩ።
ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለ12 ወራት እንዲቀጥል ከምክር ቤት አባላት ጋር እየተደራደሩ ።
የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስድስት ወራት እንዲወሰን ይፈልጋሉ።
በሌላም በኩል፤ ኩዊንስላንድ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት ሁለት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተጠቅተዋል።

