ከትናንት ረቡዕ ማለዳ አንስቶ የኒጄር ፕሬዚደንት መሐመድ ባዙምን በእገታ በቁጥጥራቸው ስር አውለው የነበሩት ወታደሮች ፕሬዚደንቱን ከስልጣን ማውረዳቸውን፣ ሕገ መንግሥቱን ማገዳቸውን፣ ማናቸውንም ተቋማትና የአገሪቱ የአየርና የየብስ ድንበሮችን የዘጉ መሆኑን በቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ አስታወቁ።
የመፈንቅለ መንግሥት አካሂያጆቹ መሪ ኮሎኔል ሜጀር አማዱ አብድራማን የመከላከያና የፀጥታ ኃይላቱ እርምጃውን በጋራ እንደወሰዱ ገልጠዋል።
የአገዛዝ ለውጥ ለማካሔድ የተነሳሱትም "የፀጥታ ሁኔታ ማሽቆልቆ፣ የምጣኔ ኃብትና ማሕበራዊ አስተዳደር ብቃት ማነስን" ለመግታት እንደሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዚደንት ባዝሙም የዩናይትድ ስቴትስ ብርቱ አጋር የነበሩ ሲሆን፤ የወታደራዊና ፀጥታ ኃይላቱን የቴሌቪዥን መግለጫ ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፕሬዚደንቱ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም ዋንጫ
ዩናይትድ ስቴትስና ኔዘርላንድስ ዛሬ ረፋዱ ላይ በዌሊንግተን ሪጂናል ስታዲየም ባደረጉት የሴቶች ዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ግጥሚያ1 ለ 1 ተለያይተዋል።

ኔዘርላንድስ በመጀመሪያው ግማሽ ጨዋታ በጂል ሩርድ አማካይነት በ17ኛዋ ደቂቃ የመሪነት ግብ ብታስቆጥርም፤ ዩናይትድ ስቴትስ በሊንድዚ ሆራን በኩል በ62ኛዋ ደቂቃ ባገባችው ግብ አቻ ለአቻ ለመለያየት በቅተዋል።

