የበጋ ኦሎምፒክ ትናንት ጁላይ 26 / ሐምሌ 19 በፓሪስ ከተማ ቀልብ በሚሰርቅ ልዩ ዝንቅ ዝግጅቱ አስደማሚና "በመጨረሻው እራት" አቅርቦቱ በክርስትና እምነት መሪዎች ዘንድ አነጋጋሪ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓትነት ተጀምሯል።
የኦሎምፒክ ዋነኛ ነበልባል በቴዲ ራይነርና ሜሪ-ሆዜ ፐርክ ተለኩሷል።

መጠናቀቂያውና የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ እሑድ ኦገስት 11 / ነሐሴ 5 ይሆናል።
በሁለት ሳምንቱ የኦሎምፒክ ውድድር 10,714 አትሌቶች በ32 የስፖርት ዘርፎች፤ በ329 ክንውኖች ተሳታፊዎች ይሆናሉ።

የስደተኛ ኦሎምፒክ ተሳታፊዎችን አክሎ፣ አውስትራሊያና ኢትዮጵያን ጨምሮ 206 ሀገራት ለወርቅ፣ ብርና ነሐስ ሜዳሎች ባለቤትነት ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ
ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው በሜልበርን ኦሎምፒክ እ.አ.አ1956 ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት 1976 (ሞንትሪያል) 1984 (ሎስ አንጀለስ) እና 1988 (ሶል) በስተቀር እስካሁኑ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ድረስ ተሳትፋለች።
ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው የኦሎምፒክ ውድድር 23 ወርቅ፣ 12 ብርና 23 ነሐስ፤ በጥቅሉ 58 ሜዳሎችን አግኝታለች።
ኢትዮጵያ ሁሉንም የኦሎምፒክ ሜዳሎች ያገኘችው በአትሌቲክስ ውድድር ነው።
ከ58ቱ ሜዳሎች ውስጥ ከአንድ በላይ የኦሎምፒክ ሜዳል ያገኙ አትሌቶች 11 ናቸው።
- ጥሩነሽ ዲባባ (2004 - 2016) 3 ወርቅና 3 ነሐስ በድምሩ 6 ሜዳሎችን በማግኘት በቀዳሚ ሥፍራ ላይ ስትገኝ፤
- ስለሺ ስህን 2 ብር (2004 - 2008) በማግኘት 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ከአንጋፋዎቹ፤
- ማሞ ወልዴ፤ 1 ወርቅ፣ 1 ብርና 1 ነሐስ (1968 - 1972) በድምሩ 3 በማግኘት 6ኛ ደረጃ፤
- አበበ ቢቂላ፤ 2 የወርቅ ሜዳል (1960 - 1964) በማግኘት 8ኛ ደረጃ ይዘው ይገኛሉ።
አውስትራሊያ በኦሎምፒክ መድረክ
አውስትራሊያ ዘመናዊ ኦሎምፒክ ከተጀመረ 1986 አንስቶ በእያንዳንዱ የኦሎፒክ 29 መድረክ የተሳተፈች ሲሆን፤ 167 ወርቅ፣ 177 ብርና 213 ነሐስ፤ በጥቅሉ 517 ሜዳሎችን አሸንፋለች።
ሙሉ የኦሎምፒክ ውድድር ሰንጠረዥ
ሙሉ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ውድድሩን እዚህ ማግኘት ይችላሉ
እንደምን መመልከት እንደሚችሉ
የአውስትራሊያ 9 ኔትዎርክ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የቴሌቪዥን ስርጭት መብቶችን አለው።
ቻናል 9 ከዜናና የብሔራዊ ራግቢ ሊግ ጨዋታዎች በስተቀር ከመክፈቻ ሥነ ሥርዓት እስከ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ድረስ በቀን ለ22 ሰዓታት ያሰራጫል።
9Gem የኦሎምፒክ ክንውኖችን እስከ ኦገስት 12 / ነሐሴ 6 ድረስ በቀን ለ24 ሰዓታት ያስተላልፋል።

