የቪክቶሪያ ምክትል ፕሪሚየር የነበሩት ጃሲንታ አለን በትናንትናው ዕለት በራሳቸው ፈቃድ ከስልጣናቸው በለቀቁት 48ኛው የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ተተኪ እንዲሆኑ በፓርቲያቸው ሌበር አማካይነት ዛሬ ረቡዕ መስከረም 16 ተመርጠዋል።
ፓርቲው የወቅቱ የሕዝብ ትራንስፖርት ሚኒስትር የሆኑትን ቤን ካሮልን በምክትል ፕሪሚየርነት አክሎ መርጧል።
የምሥራቅ ቤንዲጎ ምክር ቤት አባልና 49ኛዋ ፕሪሚየር ጃሲንታ አለን በቪክቶሪያ ታሪክ ሁለተኛዋ የሴት ፕሪሚየር ሆነዋል።
ከእሳቸው ቀደም ሲል ከ1990 እስከ 1992 የሌበር ፓርቲ መሪ የነበሩት ጆአን ኪርነር 42ኛዋና የመጀመሪያዋ የቪክቶሪያ ሴት ፕሪሚየር ሆነው አገልግለዋል።
የተሰናባቹ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ስልጣነ መንግሥት ዛሬ በምሥራቅ አውስትራሊያ መደበኛ ሰዓት አቆጣጠር 5 pm ላይ ያከትማል።