የመጀመሪያው ዙር 300,000 የአስትራዜኒካ ክትባቶች ጭነት ዛሬ እሑድ ፌብሪዋሪ 28 አውስትራሊያ ገብቷል።
አውስትራሊያ የኦክስፎርድ/አስትራዜኒካ ክትባቶችን ግዢ የፈጸመች ሲሆን 50 ሚሊየኑ ክትባቶች የሚመረቱት አውስትራሊያ ውስጥ ይሆናል።

ይህንኑ አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ሲናገሩ " አያሌ አውስትራሊያውያን የሚከተቡት ኦክስፎርድ/ አስትራዜኒካን ይሆናል። ክትባቶቹን መስጠቱም ማርች 8 ይጀምራል" ብለዋል።
ተከታቢዎች የመጀመሪያውን ክትባት ከተከተቡ በኋላ ሁለተኛውን ክትባት በ12ኛው ሳምንት ይከተባሉ።
ዩናይትድ ስቴትስ ትግራይ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ጄ ብሊንኬን ትግራይ ውስጥ እያሽቆለቆለ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ያሳሰባቸው መሆኑንና በበርካታ ቡድናት የተፈጸሙ ግድያዎችን፣ በኃይል ማፈናቀሎችን፣ ወሲባዊ ጥቃቶችን በፅኑ እንደሚያወግዙ ዛሬ ፌብሪዋሪ 28 ባወጡት መግለጫቸው አስታውቀዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ አመፅ እንዲገታ፣ ትግራይ ውስጥ የረድኤት አቅርቦት ለማድረስ ያልተገደበ ሙሉ ተደራሽነት እንዲኖር፣ በሪፖርቶች የተጠቀሱ የሰብ ዓዊ መብቶች ጥሰቶች ሁሉ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ምርመራዎች እንዲካሄድባቸውና ለዚያም የግድ ተጠያቂነት እንዲኖር በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መነጋገሯን ገልጠዋል።
እንዲሁም፤ ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በውጭ ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል ሙሉዕ የረድኤት አቅርቦት ተደራሽነት እንዲኖር፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ለመመርመርና ሙሉ ተጠያቂነትም እንዲኖር የሚደረግ መሆኑን አስመልክተው ያወጡትን መግለጫ በመልካምነቱ እንደምትቀበለው ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህ ዕውን እንዲሆን በጋራ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግቦች እንዲመቱም አብራ እንደምትሠራና የUSAID አደጋ ታዳጊ ግብረ መልስ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚሄድና በሕይወት መታደግ እገዛዎቹ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።
አክለውም "የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች በአስቸኳይ መውጣት አስፈላጊ የመጀመሪያ እርምጃዎች ናቸው" ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ሽርካዎች በተለይም የአፍሪካ ሕብረትና የአካባቢው ወዳጆች፤ የተመድና ሌሎች አካላትንም አካትቶ ትግራይ ውስጥ ያለውን ቀውስ ዕልባት ለማበጀት የግብራዊ ምላሽ ጥሪ አቅርበዋል።
በማጠቃለያቸውም "ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ዘላቂ ወዳጅነት በመገንባት ፀንታ ትቀጥላለች" ብለዋል።

