የሜይ 21 / ግንቦት 13 አገር አቀፍ ምርጫ በሌበር ድል አድራጊነት መጠናቀቅና ለመንግሥትነት መብቃት የሊብራል/ናሽናልስ ፓርቲዎችን ለተቃዋሚ ቡድንነት ዳርጓል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ድል በተነሱበት ምሽት ከሊብራል ፓርቲ መሪነታቸው መነሳታችውን ማስታወቃቸው በምትካቸው አዲስ መሪን መምረጥ ግድ አሰኝቷል።
የሊብራል ፓርቲ ፌዴራል ምክር ቤት አባላት ነገ ሰኞ በሚያደርጉት ስብሰባ የቀድሞውን የአገር ውስጥ ጉዳይና መከላከያ ሚኒስትር ፒተር ዳተንን ያለ ተቀናቃኝ በተቃዋሚ ቡድን መሪነት ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ሊብራል ፓርቲ በቀኝ ክንፍ አክራሪነት የሚወቀሱትን አቶ ዳተን መሪው ለማድረግ ማሰብ ከወዲሁ 'ፓርቲው አሁንም ከስህተቱ አልተማረም፤ ጥለውት የሔዱትን፣ የቀድሞ ደጋፊዎቹንና የአውስትራሊያውያንን ድምፅ አልሰማም የሚያሰኙ ትችቶችን አሰንዝሯል።
ሆኖም በአብላጫ የፓርቲው አባላትና ዝንፈት የለሽ ደጋፊዎቹ ዕይታ አቶ ዳተን 'የወግ አጥባቂዎችን ዕሴቶች የሚያስከብሩ፣ በመጪው 2025 አገር አቀፍ ምርጫ ወቅትም ፓርቲያቸውን ለድል የሚያበቁ ጠንካራ መሪ ናቸው' እያሰኘ ነው።
የፒተር ዳተን የተቃዋሚ ቡድን መሪ ሆኖ ያለተቀናቃኝ ነገ ሰኞ በሊብራል ፓርቲ ይሁንታ የማግኘት ሁኔታ በሌበር በኩል አሉታዊ አስተያየትን ሰንዝሯል።
አዲሱ በጅሮንድ ጂም ቻልመርስ ባለፈው ረቡዕ የሊብራል ፓርቲ ከቅዳሜው ምርጫ ውጤት ምንም እንዳልተማረ ጠቅሰው "ፒተር ዳተን ሰዎች ስኮት ሞሪሰን ላይ ያልወደዷቸውን ባህሪያት የተላበሱ ናቸው" ብለዋል።
አቶ ዳተን በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ወቅቶች በአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ብሔራዊ የይቅርታ ቀን ለመገኘት አለመፍቀድ፣ የሊባኖሳውያን ወደ አውስትራሊያ እንዲመጡ መፍቀድ ስህተት እንደነበር መናገር፣ የሜልበርን ፀጥታ 'ከአፍሪካ ወሮበሎች ' ጋር ማገናኘት፣ ቻይናን አስመልክቶ አውስትራሊያ ለጦርነት እንድትዘጋጅ የማነሳሻ ቃላቶችን መጠቀም በቀኝ አክራሪነት አቋም ጎልተው የሚጠቀሱባቸው ትችቶች ናቸው።
የአቶ ዳተን ምክትል ምናልባትም የቀኝ ክንፍ አንጃ ውስጥ ያሉት የቀድሞዋ የአክባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ሱዛን ሊ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሎ እየተነገረ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በነገው ዕለት የናሽናልስ ፓርቲ በፊናው የመሪ ምርጫ ያካሂዳል።

በመሪ ምርጫ ሂደቱም የወቅቱ የናሽናልስ መሪና የቀድሞውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባርናቢ ጆይስ ተቀናቅነው የናሽናልስ ምክትል መሪ ዴቪድ ሊትልፕራውድ፣ የቀድሞው የናሽንልስ መሪ ማይክል ማኮርማክ እና የቀድሞው የጡረተኛ ወታደሮች ጉዳይ ሚኒስትር ዳረን ቸስተር ራሳቸውን ለአመራር ምርጫ አቅርበዋል።
ፊጂ - አውስትራሊያ
የፊጂ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲሷ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንን የአየር ንብረት ለውጥ አቋም መክላታቸው እንዳስደሰታቸው ገለጡ።
የፊጂ መሪ ፍራንክ ባይኒማህራማ ከፔኒ ዎንግ ጋር ያካሄዱትን ስብሰባ "ግሩም ስብሰባ" በማለት አወድሰው በማኅበራዊ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

አቶ ባይኒማህራማ አክለውም "ፊጂ የማንም ጓሮ አይደለችም። እኛ የፓስፊክ ቤተሰብ ነን። የኛ ትልቁ ስጋት ጂኦፖለቲክስ አይደለም፤ የአየር ንብረት ለውጥ ነው" ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዎንግ እንደ አውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራሳቸውን ችለው ጉብኝት ሲያደርጉ የፊጂ ጉዟቸው የመጀመሪያው ነው።
ሳሞኣ - ቻይና
ሳሞኣ ከቻይና ጋር ስምምነት ከፈረሙ የፓስፊክ አገራት አዲሷ ታካይ አገር ሆናለች።
የሳሞኣ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊአሜ ናኦሚ ማታፋ በተገኙበት የሁለቱ አገራት ስምምነት ለፊርማ የበቃው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የፓስፊክ ጉብኝትን ተከትሎ ነው።
ስምምነቱ በእስያ አገራት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት አሳድሯል።

የሳሞኣ ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ ባደረጉት መግለጫ ስምምነት ያለመው በቻይናና ሳሞኣ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደሆነ ገልጠዋል።
መግለጫው አክሎም በሁለቱ አገራት መካከል በተካሔደው ስብሰባ ተነስተው ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ ቀጣናውን አስመልክቶ ቁልፍ የተባሉ የአየር ንብረት ለውጥ። ወረርሽኝ፣ ሰላምና ፀጥታን የመሳሰሉት "የጋራ ጥቅሞችና ስጋቶች" መሆናቸውን ጠቅሷል።

