ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችም በምርቃቱ ተገኝተዋል።
በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ እንደተናገሩት "ህፃናትና ወጣቶች አካላቸውና አዕምሯቸው የሚዳብርበት ስፍራ በመሃል ከተማ ተገንብቷል። እንደ ወዳጅነት ፓርክ ምዕራፍ ሁለት ፕሮጀክት በየክልሉ ለህፃናት የሚሆኑ ሥራዎች ያስፈልጋሉ" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም "ፓርኩ በውጭ አገራትና በፊልም እናየው የነበረውን ዘመናዊ መዝናኛ እዚሁ አገራችን ላይ ልጆቻችን እንዲጠቀሙበት ያደረገ ነው" ያሉ ሲሆን "መጪው ትውልድ አገሩን እየወደደ እንዲያድግ የሚረዳ ፕሮጀክት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ አካባቢዎች ማስፋፋት ያስፈልጋልም" ብለዋል ፡፡
ፓርኩ ስፖርትን፣ ጨዋታንና ማኅበራዊ መስተጋብርን ያቀናጀ ሲሆን ልጆች እየተጫወቱ ሳይንስና ቴክኖሎጂን መለማመድ ያስችላቸዋል።
"ወጣቶች ያነብባሉ፣ ደግሞም ስፖርት ይሠራሉ። ወላጆችና አያቶች ከልጆቻቸው ጋር መጥተው ማኅበራዊ ልምዳቸውን ይለዋወጣሉ። አዲስ ተጋቢዎች በሠርግ ዐጸዱ ጋብቻቸውን ይመሠርታሉ።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለች እንድትሆን የተሻለ ትውልድ እያፈራን እንቀጥላለን"ም ብለዋል።

Adanech Abiebie, Mayor of Addis Ababa (L), Ethiopia's Prime Minister Abiy Ahmed (C), and Zinash Tayachew, First Lady of Ethiopia (R). Credit: PMOE
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ፊት ለፊት አንስቶ ወደ አሮጌው ቄራ መውረጃና የእሪ በከንቱ አካባቢዎችን ያጠቃለለው ፓርኩ ለአንድ ሳምንት ለጎብኝዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተገልጿል።
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]