የአውስትራሊያ ነባር ዜጋ ድምፃዊ፣ ተራኪና አንቂ አርቺ ሮች ትናንት ማምሻውን በ66 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
የጉንዲትጃማራ እና ባንድጃላንግ አረጋዊ፣ ገጣሚና ተራኪው ለረጅም ጊዜያት በጠና ሕመም ተይዞ የነበረ ሲሆን ለሕልፈተ ሕይወት የበቃው በቪክቶሪያ ቤዝ ሆስፒታል በቤተሰቡና ወዳጅ ዘመዶቹ ተከብቦ ነው።
የድምፃዊው ወንድ ልጆች አሞፅ እና ኢባን ሮች በአባታቸው ሕልፈት ሕይወት ብርቱ ሐዘን የተሰማቸው ቢሆንም፤ በሕይወት ዘመኑ በከወናቸው ማለፊያ ተግባራት የሚኮሩ መሆኑን ባወጡት የሐዘን መግለጫ ገልጠዋል።
አክለውም፤ አባታቸው አስታራቂና አንድነትን አጎልባች ኃይል እንደነበረና በሙዚቃውም ሰዎችን በአንድ ላይ እንዳቆመ አመላክተዋል።
ሮች ከሚታወቅባቸው ዘፈኖቹ አንዱ የተሰረቁ ትውልዶችን የሕይወት ውጣ ውረድ የሚያንፀባርቀው "Took the Children Away" የሚለው ነው።
ለድምፃዊ ሮች የሐዘን መልዕክቶቻቸውን ካስተላለፉት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚና የቪክቶሪያው ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ይገኙበታል።
ቤተሰቡም የአርቺ ሮች ስም፣ ምስልና ሙዚቃ የሕይወት ውርሰ አሻራው ሆኖ እንዲቀጥልና ለሌሎች መንፈስ ማነቃቂያነትም ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃዳቸውን ሰጥተዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ
ፖፕ ፍራንሲስ የዕድሜያቸው መግፋትና የአካላዊ ጤናቸው መዳከም የመሥራት አቅማቸውን የሚያስተጓጉል ከሆነ በጡረታ ለመገለል ዕሳቤ ያላቸው መሆኑን ጠቆሙ።
የ85 ዓመቱ ፖፕ ይህን ያሉት በካናዳ ነባር ዜጎች ሕፃናት ተማሪዎች ነጠቃ ላይ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የነበራትን ሚና አስመልክቶ ይቅርታን ለመጠየቅ ሔደው አንድ ሳምንት ቆይተው ወደ ሮም እየተመለሱ ሳለ ነው።
ፖፕ ፍራንሲስ የጉልበት ስንጥቃት ባስከተለባቸው ብርቱ ሕመም በተሽከርካሪ ወንበር አለያም በመመርኮዣ ለመንቀሳቀስ ግድ ተሰኝተዋል።

Pope Francis is helped to his seat beside Canadian Prime Minister Justin Trudeau as he arrives in Canada, on July 24, 2022 in Edmonton, Canada. Source: Getty
ቀደም ሲል ለቀዶ ሕክምና ማደንዘዣ ሲወስዱ ባደረሰባቸው የጎንዮሽ ጉዳት ሳቢያም ዳግም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም።
ፖፕ ፍራንሲስ ምንም እንኳ የካናዳው ጉዞ የፈተናቸው ቢሆንም ቀደም ሲል ለጉብኝት ቃል ወደ ገቡላቸው አገራት ደቡብ ሱዳን፣ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ ሊባኖስ እና ምናልባትም ካዛኪስታንንም በማከል ቃላቸውን ከማክበር ወደ ኋላ እንደማይሉ አመላክተዋል።
በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የ600 ዓመታት ታሪክ ውስጥ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው በመንበረ ፖፕ ተሰይመው በመቆየት ፈንታ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2013 በፈቃዳቸው የተሰናበቱ ፖፕ ቤኔዲክት ናቸው።