የሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ዛሬ ሐሙስ ምሽት አውስትራሊያ ፓርላማ ውስጥ አማራጭ የበጀት ምላሽ ንግግር ያደርጋሉ።
የሞሪሰን መንግሥት ማክሰኞ ምሽት የ2022/23 ዓመታዊ በጀት ይፋ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አቶ አልባኒዚ ከመንግሥት የተሻለ አማራጫ በጀት እንዲያቀርቡ የገፉ ሲሆን፤ የተቃዋሚ ቡድን መሪው የመንግሥት በጀት ድምፅ መግዣ የፖለቲካ ሰነድ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
የፌዴራል ምርጫ ቀን በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ይቆረጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የሩስያና ሕንድ ባንኮች
የሕንድ መንግሥት በሩስያ ብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀውን የሁለትዮሽ የክፍያ ሥርዓት ላይ ለመወያየት በሯን ከፍታለች።
ሕንድ ከሩስያ ነዳጅና የጦር መሣሪያዎችን መግዛት ትሻለች።
ሕንድ የሩስያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሥርዓትን ለመጠቀም ገና ከውሳኔ ላይ አልደረሰችም።
ሆኖም የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ለሁለት ቀናት ቆይታ ዛሬ ማርች 31 ሕንድ ሲገቡ የሁለቱ አገራት የመወያያ አጀንዳ ይሆናል።
ሕንድ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ አውስትራሊያና ጃፓን ጋር ተሳታፊ ከሆነበችበት የጋራ አራትዮሽ ቡድን ሩስያ ላይ ጠንካራ አቋም እንድትይዝ ዲፕሎማሲያዊ የማግባባት ጫና ቢገጥማትም ከሩስያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት ሳታቋርጥ ቀጥላለች።
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ጎርፍ
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ዳግም የተከሰተው ጎርፍ የሊዝሞር ነዋሪዎች ዳግም ቀዬአቸውን ለቅቀው እንዲወጡ ግድ አሰኝቷል።
ማክሰኞ ዕለት ሊዝሞር ዋይራላህ መንገድ ላይ ሆንዳ ካፕቲቫ መኪናዋ ውስጥ ሳለች በጎርፍ ተከብባ የነበረችዋ የ55 ዓመቷን አኒታ ባርኬል የደረሰችበት ባለመታወቁ ፍለጋ ቀጥሏል።
የSES ረዳት ኮሚሽነር ኒኮል ሆጋን 20 ቀዬን ለቅቆ የመውጣት ትዕዛዞች ለ27 ሺህ ያህል ነዋሪዎች መስጠቱን ለABC ገልጠዋል።
ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዛሬ ሐሙስ 5:30 pm ለአውስትራሊያ ፓርላማ ንግግር ያደርጋሉ።

