የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ የአረጋውያን ክብካቤ ኢንዱስትሪን ለማሻሻል $2.5 ቢሊየን እንደሚመድቡ ዛሬ ምሽት ማርች 31 አስታወቁ።
የሌበር ፓርቲ የአረጋውያን ክብካቤን ለማሻሻል በአምስት ዘርፎች ላይ እንደሚያተኩር ገልጧል።
- ሬጂስተርድ ነርሶች በቀን ለ24 ሰዓታት በአረጋውያን መጠወሪያ ሥፍራ እንዲገኙ ማድረግ
- ተጠዋሪዎች በቀን የሚያገኙት የክብካቤ ሰዓታትና የተከባካቢዎችን ቁጥር መጨመር
- ለአረጋውያን ክብካቤ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ ማድረግ
- የተሻለ ምግብ ለተጠዋሪዎች ማቅረብ
- ተጨማሪ የገንዘብ ድጎማ መስጠት
አቶ አልባኒዚ እነዚህ እርምጃዎች የአረጋውያን ክብካቤ ኢንዱስትሪ ገጥመውት ያሉትን ቀውስ ለመክላት ያስችላሉ ብለዋል።
አያይዘውም የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ የደመወዝ ጭማሪ ዕቅዳቸውን አስታውቀዋል።
የሥራና የገቢ ምንጮችን ከፍ የሚያደረጉ ዕድሎችን ለመፍጠርም የሌበር ፓርቲ ለታዳሽ ኃይል፣ የፋብሪካ ሥራዎች፣ መሠረተ ልማት፣ የትምህርትና ስልጠና ዕድሎችን ማስፋፋትና ለአነስተኛ አቅም ተመጣጣኝ የሆኑ ሙዋዕለ ሕፃናት ላይ ሙዋዕለ ንዋይ እንደሚያፈስ ገልጠዋል።
አክለውም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መንግሥት በጀት ከምርጫ በፊት የድምፅ መግዣ ገንዘብን መርጨት ላይ እንጂ የኑሮ ውድነትን ችግር የሚፈታ ዘላቂ መፍትሔ ላይ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።
ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ዛሬ ማምሻውን ለአውስትራሊያ የሕዝብ ተወካዮችና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት በጣምራ የዩክሬይንና ሩስያን ጦርነት አስመልክተው ንግግር አደረጉ።
አቶ ዜሌንስኪ ንግግራቸውን ያሰሙት በበይነ መረብ አማካይነት ሲሆን ከንግግራቸው በፊትና በኋላ የፓርላማ አባላቱ ቆመው አድናቆትና ድጋፋቸውን በጭብጨባ ገልጠውላቸዋል።
ፕሬዚደንቱም የአውስትራሊያን አስተዋፅዖዎች አስመልክተው ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ተጨማሪ እርዳታ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።

አውስትራሊያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችንና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬይን ብትረዳ አገራቸው ከሩስያ ጋር ገጥማ ላለቸው ጦርነት ከፍተኛ እገዛ እንደሚሆን ተናግረዋል።
እንዲሁም የአውስትራሊያ መንግሥት በሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንዲጥል ጠይቀዋል።
የፕሬዚደንቱን ጥሪ ተከትሎም የአውስትራሊያ መንግሥት ማምሻውን ለዩክሬይን ጦር መርጃ የሚውል $25 ሚሊየን መስጠቱንና በጥቅሉም $116 ሚሊየን ወታደራዊ እርዳታ ማድረጉን ይፋ አድረጓል።

