የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኦገስት 27, 2022 / ነሐሴ 21, 2014 ባወጣው መግለጫ ሕወሓት የሰው ኃይል ማዕበል በመጠቀም የቆቦ ከተማን በበርካታ አቅጣጫ እያጠቃ መሆኑንና ሠርጎ ገቦችንም በማሥረግ የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ አመላክቷል።
አያይዞም፤ ይህንኑ ምክንያት በማድረግ "የሕዝብን ከፍተኛ ፍጅት ለማስወገድ ሲባል የመከላከያ ኃይል የቆቦ ከተማን በመልቀቅ እና ወደ ኋላ መጥቶ ለመከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎችን ለመያዝ ተገዷል" ሲል አስታውቋል።
ሆኖም ሕወሓት "በሕዝብ ማዕበል ማጥቃቱን ካላቆመ መከላከያ ሕጋዊ፣ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታውን ለመወጣት የሚገደድ ይሆናል" በማለት የመንግሥትን ቀጣይ እርምጃ አመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በትግራይ የብዙሃን መገናኛ በኩል ባለፉት ሶስት ተከታታይ ቀናት የተካሔዱ ውጊያዎችን ተከትሎ ቆቦ ከተማን በማከል ጉጉዶ፣ ፎኪሳ፣ ዞብል፣ መንደፈራ፣ ሮቢት፣ ሺህዎች ማርያምና ተኩለሽ በሕወሓት ጦር ቁጥጥር ስር ለመሆን መብቃታቸው ተዘግቧል።
ዘገባውን አስመልክቶ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ምንጮች ማረጋገጫ አልተሰጠም።