ሕወሓት በመንግሥት የአየር ጥቃት የሕፃናት ሕይወት ማለፉን ሲያመለክት፤ በመንግሥት በኩል ማስተባበያ ተሰጠ

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መንግሥትና ሕወሓት ከግጭት ተገትተው ወደ ሰላም ንግገር እንዲመለሱ ጥሪ እያቀረበ ነው

A 80-year-old woman, who fled the violence in Ethiopia's Tigray region.jpg

A 80-year-old woman, who fled the violence in Ethiopia's Tigray region፣ on June 19, 2021. Credit: YASUYOSHI CHIBA/AFP via Getty Images

የትግራይ የውጭ ጉዳዮች ቢሮ ባወጣው መግለጫ ኦገስት 26, 2022 / ነሐሴ 20 - 2014 በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር 12:30 pm ላይ በኢትዮጵያ መንግሥት በተሰነዘረ የአየር ጥቃት በልጆች መጫወቻና ሙዋዕለ ሕፃናት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

የሟቾችና ቁስለኞችን ቁጥር ያላሰፈረው መግለጫ አያይዞም፤ የአየር ጥቃቱ የተሰነዘረው ወታደራዊ ዒላማዎች ባሉበት አካባቢ ሳይሆን በመኖሪያ ቀዬ ዙሪያ እንደሆነ ጠቅሶ፤ በሳቢያውም "የንፁሃን ሕፃናትና አዋቂዎች ሕይወቶች በጣሙን በዘቀጠ መንገድ አካላቶቻቸው ለቁርጥራጭነት" ተዳርጓል ሲል አመልክቷል።

ይሁንና በተለያዩ ሪፖርቶች የሟች ሕፃናት ቁጥር ከሁለት እስከ ሰባት መድረሱ ተጠቅሷል።

በመቀሌ የአይደር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ክብሮም ገብረሥላሴ ደስታ ሆስፒታላቸው የሁለት ሕፃናትን ሕልፈተ ሕይወት መመዝገቡን በቲዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።


በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ግና የሕወሓት መግለጫ ሐሰት ላይ የተመሠረተ እንደሆነና መንግሥት ከወታደራዊ ዒላማዎች ውጪ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳልሰነዘረ ማስተባበያ ተሰጥቷል።

በኖቬምበር 2020 በሕወሓትና የፌዴራል መንግሥቱ መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውንና ከሁለት ሚሊየን በላይ ቀዬአቸውን ለቅቀው ወደ ሌሎች ሥፍራዎ እንዳመሩ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ባለስልጣን ተናግረዋል።

በመንግሥትና ሕወሓት መካከል የነበሩ ግጭቶች ነሐሴ 19 ንጋት ላይ ዳግም እስከተቀሰቀሰ ድረስ ለአራት ወራት ያህል ጋብ ብሎ የነበረና ከቶውንም ሁለቱ ወገኖች ፊታቸውን ወደ ሰላማዊ ድርድር ይመልሳሉ የሚል ተስፋ አሳድሮ ነበር።

የዳግም ግጭቱን መቀስቀስ በመስማታቸው "ጥልቅ ኃዘንና ድንጋጤ" የተሰማቸውን መሆኑን በዕለቱ የገለጡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ፤ ሁለቱ ወገኖች በግጭት ፈንታ ወደ አስቸኳይ ተኩስ አቁምና የሰላም ንግግር እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በበኩሉ "ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "ሁለቱ ወገኖች" ከሚል ፍርደ ገምድል ጥሪ ተላቅቆ መንግሥት ወደያዘው የሰላም አማራጭ ሕወሓት እንዲመጣ ግፊት እንዲያደርግ፤ ይህ ካልሆነና ሕወሓት ጥቃቱን የሚቀጥል ከሆነ መንግሥት በሕግ የተጣለበትን ግዴታ ለመወጣት ሲል ማንኛውንም እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ ይሆናል" ሲል የመንግሥትን የሰላም ጥሪና የኃይል እርምጃ ማስጠንቀቂያ አያይዞ አስታውቋል።

የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በፊናቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ሰላም ጥሪ ሲያቀርብ መንግሥት በመቀሌ ሙዋዕለ ሕፃናት አካባቢ የአየር ጥቃት እንደሰነዘረ አመላክተዋል።


Share

Published

Updated

By Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service