ተቃውሞ በዩናይትድ ስቴትስ
በአፍሪካዊው - አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ሞት ሳቢያ ዩናይትድ ስቴትስ ውጥረትና ንዴትን ባዘሉ የተቃውሞ ሰልፎች ተንጣ ተጨማሪ ምሽት አሳልፋለች።
የተቃውሞ ሰልፎቹ በ30 ከተሞች ውስጥ የተካሔዱ ሲሆን፤ በሎስ አንጀለስ የ500 ሰዎችን እሥራት፤ እንዲሁም ኒው ዮርክ ውስጥ ቃጠሎ፣ ዘረፋና ሁከትን አስከትለዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞው የተቀሰቀሰባት ሚኒሶታ ገቨርነር ቲም ዎልትዝ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሆነውን 13 000 የሙሉ ናሽናል ጋርድ አባላትን ለፀጥታ አስከባሪነት ተግባር ጠርተዋል።
አቶ ዎልትዝ ሰዎች ለተውቃውሞ ሰልፍ እንዳይወጡና ፍትሕ ብይን እንደሚያገኝ ሲያስቡ፤
"የዛሬው ሥራችሁ እንዲሆን የምጠይቀው - ወደ ቤታችሁ እንድትሔዱ፣ ጎዳናዎች ላይ እንዳትገኙ ነው። ዛሬ ማምሻውን ወደ ጎዳናዎች የሚወጡ ሰዎች ይህን ጥሪ እንዲቀበሉ ነው። ይህ ፈታኝ ሁነት ነው። እኒህ ሰዎች የሚሹት ምንም ሳይሆን፤ ማኅበረሱ ተከፋፍሎ ማየት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ቀውስና ፍርሃትበመላው የቴሌቪዥን ጣቢያ ስክሪኖችንና የጋዜጦችን ገጽ ሞልተው መመልከትን ነው። እኛ ይህን አንሰጣቸውም" ብለዋል።
የቤት ውስጥ ጥቃት ሞቶች
ፖሊስ በምዕራባዊ ሲድኒ ሁለት በሃያዎቹ ዕድሜ ያሉ ወጣቶች ሕልፈተ ሕይወት ከቤት ውስጥ ጥቃት ጋር ተያይዥነት አለው ብሎ እንደሚያምን ገለጠ።
ዋና መርማሪ ኢንስፔክተር ፖል ቲክነር እንዳሉት፤ ማውንት ድሩት አካባቢ ካለ አንድ የቢድዌል መኖሪያ ቤት እንዲደርስ ለፖሊስ በተደረገ ጥሪ አንድ ወንድና አንዲት ሴት በስለት ተወግተው ማግኘቱን ሲናገሩ፤
"ፖሊስ የአንዲት የ22 ዓመት ሴት አካል በርካታ ጊዜያት በስለት ተወግቶ አግኝቷል። እንዲሁም አንድ የ22 ዓመት ወንድ ከቢድዌል ደረቱ ላይ ራሱን በራሱ በስለት ወግቶ አግኝቷል። ሴቷ በሂሊኮፕተር ወደ ዌስትሚድ ሆስፒታል ተወስዳ ቀዶ ሕክምና ተደርጎላታል። ሕይወቷን ለማትረፍ ቀዶ ሕክምና ቢደረላትም ሕይወቷ አልፏል። ወንዱ እዚያው በተገኘበት ሥፍራ ነፍሱ ወጥታለች። በዚህ ወቅት የምንፈልገው ሌላ ተጠርጣሪ የለም። እውነታ ነው ብለን የምንመለከተው ወንዱ ሴቷን ደጋግሞ ለበርካታ ጊዜያት በስለት መውጋቱና ራሱንም መውጋቱን ነው" ሲሉ የፖሊስ ምልከታን አስታውቀዋል።
ይህ ሁነት ስጋቶችን ያሳደረብዎ ከሆነ ወደ ቤተሰብ ጥቃት የምክር አገልግሎትን በ1800 RESPECT ያግኙ ። አሊያም በ1800 737 732 ወይም Lifeline ዘንድ በ 13 11 14 ደውለው ያነጋግሩ።
የኅዋ መጠቃ
ዩናይትድ ስቴትስ በኅዋ መጠቃ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በግል የተያዘ የኅዋ በረራን በተሳካ መልኩ አከናውናለች።
የኅዋ መጠቃው የተሳካው በናሳና ቢሊየነር ኢሎን ማስክ ስፔስ -ኤክስ ኩባንያ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገ ሙከራ ነው።
ምንም እንኳ ነጎድጓድ ሊያውካቸው ቢሞክርም ጠፈርተኞቹ ሮበርት ቤህንኬንና ዳግላስ ሃርሊ ወደ ኅዋ መጥቀው ጉዟቸውን ወደ ዓለም አቀፍ የኅዋ ጣቢያ አቅንተዋል።
የቫይረስ ገደቦች
ከነገ ሰኞ ጀምሮ የተወሰኑ ስቴቶች ተጨማሪ የኮቪድ - 19 ገደቦችን የማላላት ዋዜማ ላይ ባሉበት ወቅት አውስትራሊያ ለዜሮ በተጠጋ አዲስ በቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥርን አስመዝግባለች።
በትናንትናው ዕለት ከመላው አውስትራሊያ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተከሰቱባት ቪክቶሪያ ብቻ ናት።
በነገው ዕለት ካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ቤተ መጽሓፍት፣ ጋለሪዎች፣ ሙዚየሞች፣ የመዝናኛ ፓርኮች፣ የመጸለያ ሥፍራዎች፣ የውበት ክሊኒኮች፣ የጥፍር ሳሎኖችና መታሻዎች በ20 ተጠቃሚዎች ውስን ሆነው ግልጋሎታቸውን መስጠት ይጀምራሉ።
በተጨማሪም፤ ቪክቶሪያውያን የዕረፍት ቤቶቻቸውን፣ የቱሪስት መኝታ ቤቶችን፣ ካራቫን ፓርኮችንና የካምፕ ሥፍራዎችን መጠቀም ይችላሉ።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ መጠጥ ቤቶች፣ የውበት ሳሎኖችና ሙዚየሞች ክፍት ይሆናሉ።
ነዋሪዎች ኒው ሳዝ ዌይልስ ውስጥ ለሽርሽር መጓጓዝ ይችላሉ።
የጸሎትና የቀብር ሥፍራ ታዳሚዎች ቁጥር እስከ 50 ከፍ ይላል።

