አዲሱ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ቃለ መሃላ ከፈፀሙ ጥቂት ሰዓታት በኋላ ትንናት ወደ ቶኪዮ አምርተው ዛሬ ቶኪዮ ላይ በተካሔደው የአራትዮሽ የፀጥታ መድረክ ጉባኤ ላይ ታድመዋል።
አውስትራሊያን ጨምሮ የመድረኩ ታዳሚዎች፤ የዩናይትድ ስቴትስ፣ ጃፓንና ሕንድ መሪዎች ናቸው።
በመሪዎቹ የአንድ ቀን ጉባኤ ላይ አራቱ አገራት የቻይናን የኢንዶ ፓስፊክ ተፅዕኖ ለመቀነስ በይበልጥ ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸው በአቶ አልባኒዚ በኩል ማሳሰቢያ ቀርቧል።

አቶ አልባኒዚ ያለፈው የሞሪሰን መንግሥት ከቻይና ጋር ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ደጋግሞ ሲያነሳ ስለበረው የፀጥታ ጉዳይ በጋዜጠኞች ተጠይቀው ሲመልሱ " በቀጣናው የምንሻው ሰላምና መረጋጋትን ነው። ያንንም ተገቢ በሆነ ዲፕሎማሲያዊ ሂደት ቀጣናዊ ግንኙነትን መገንባት ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ለአዲሱ ተመራጭ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸው ላይም አያይዘው "ቻይና ያለፈውን ወደ ኋላ ትታ ወደፊት በመመልከት፣ እኩል መከባበርና የጋራ ትሩፋት መርሆችን በመመርኮዝ፣ የቻይና አውስትራሊያ ስትራቴጂያዊ ወዳጅነን ያካተተ የሰከነ ልማትን ከፍ በማድረግ ከአዲሱ የአውስትራሊያ መንግሥት ጋር ለመሥራት ትሻለች" ብለዋል።
በሌላም በኩል በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ሊ የሚመራ ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ሰለሞን ደሴቶችን ጨምሮ ስድስት የፓስፊክ አገራትን ይጎበኛል።

ጉብኝቱን አስመልክቶ የሰለሞን ደሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ሶጋቫሬ አገራቸው "ከቻይና ጋር የምታደርገው የልማት ወዳጅነት በታሪካችን ውስጥ በጣሙን ወሳኝ ነው" ብለዋል።
የቻይና ልዑክ ቡድን የፓስፊክ አገራቱን ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ባሉት ቀናት ውስጥ ቀጣናዊ ጉብኝት ያካሒዳል።

