ቫይረስ አንዛክ
አውስትራሊያውያን የአንዛክ ቀን መታሰቢያን በየደጃቸውና ቤታቸው ውስጥ ሆነው ጎሕ ሲቀድ አከበሩ።
ኮሮናቫይረስ ካለፉት አሠርት ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተለምዷዊ በሆነ መልኩ ተዘክሮ እንዳይውል ግድ አሰኝቷል።
የአንዛክ ቀን ሠልፎች አውስትራሊያ ውስጥ የዘንድሮውን ጨምሮ ሳይከናወኑ የዋሉት ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ መጨረሻ ላይ ሳይከበር የቀረው በ1942 የስፓኒሽ ወረርሽ ወቅት ነበር።
የቬይትናም ዘማቹ ጆን ሺፐርድ ክብረ በዓሉን አስመልክተው ሲናገሩ "የአንዛክ መንፈስና የመስዋዕትነት ዋጋን በኮቪድ - 19 ወረርሽ ወቅትም ቢሆን አስቦ መዋሉ በጣሙን ጠቃሚ ነው" ብለዋል።
አንዛክ - በፖለቲከኞች አንደበት
የአንዛክ ክብረ በዓል የአውስትራሊያ መሪዎች በተገኙበት ካንብራ ውስጥ በብዙኅን መገናኛ ቀጥታ ሥርጭት ተላልፏል።
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር "ምንም እንኳ በዚህ ዓመት ክብረ በዓሉ ቢስተጓጎልም፤ አውስትራሊያውን በያሉበት የወደቁትን ሰማዕታት አስበው ውለዋል" ሲሉ የአንዛክ መንፈስ መደናቀፉን እንጂ አለመዘንጋቱን ተናግረዋል።
የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን በበኩላቸው ደጃፋቸው ላይ ጎሕ ሲቀድ ከዕጮኛቸውና የዕጮኛቸው አባት ጋር ሆነው ዘክረዋል።
መታሰቢያውን አስመልክተው ሲናገሩም "እውነት ነው፤ ዝክረ በዓሉን ለማሰብ አዲስ መንገዶችን መፈለግ ነበረብን። ዓላማው ግና አንድ ነው። በዛሬዋ ዕለት አናዛክን አስበን ስንውል፤ ሰላም ላይ ተስፋን ጥለን ነው" ብለዋል።
ቫይረስ - አውስትራሊያ
ታዝማኒያ ውስጥ ሕይወታቸው ሲያልፍ አሥረኛው የሆኑት ግለሰብ፤ አውስትራሊያ ውስጥ በኮቪድ -19 ሕይወታቸውን ያጡትን ሰዎች ቁጥር 80 አድርሶታል።
የ90 ዓመቱ የታዝማንያ ነዋሪ ሕይወታቸው ያለፈው በትናንትና ው ዕለት ሜሪሲ የማኅበረሰብ ሆስፒታል ውስጥ ነው።
አውስትራሊያ ውስጥ እስከ ኤፕሪል 25 ማለዳ ድረስ 6,687 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ ከእነሱም ውስጥ 5,273 አገግመዋል፤ 487,000 የቫይረስ ምርመራዎች ተካሂደዋል።

