ተፈጥሯዊና ባሕላዊ ዝናቦችን ምን አዛመዳቸው?

*** በሰሞኑ “ኢትዮጵያ ሰው-ሰራሽ ዝናብ አዘነበች” የሚለውን ዜና አስመልክቶ በርካታ ቀልድና ቁም ነገሮች በማሕበራዊ ሚድያ ተንሸራሽረዋል። ይህንን ጽሁፍ እንድጽፍ የኮረኮረኝ አባባል “በባህላዊ መንገድ'ኮ በሃገራችን ለበጎም ይሆን ለተንኮል ሲባል ዝናብን ሊያስጀምሩ አልያም ሊያስቆሙ የሚችሉ በርካታ “ተአምረኞች” እያሉ ለምን የደመና መዝራት (cloud seeding) ቴክኖሎጂ አስፈለገ?” የሚለው ወሬ ነው።

artificial precipitation

Aircraft prepares to spray calcium oxide on a mission to generate artificial precipitation. Source: Getty

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ትውስታ ነበረኝና አጋጣሚውን ተንተርሼ እንደሚከተለው ለማጋራት ወደድሁ።

የሶስተኛ አመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ ለቀናት የሚዘልቅ የስዕል ኤግዚቢሽን አምስት ኪሎ በሚገኘው የድህረ ምረቃ አዳራሽ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። ለየት የሚያደርገው ታዋቂው ሰአሊ አፈወርቅ ተክሌ የመገኘታቸው ዜና ነው። እርሳቸው በቦታው ተገኝተው ለጎብኚና አድናቂዎች ፊርማ ያኖራሉ፤ ለስዕሎቻቸውም ማብራሪያ ይሰጣሉ በተበላበት ቀን ከጓደኞቼ ጋር በስፍራው ተገኘሁ።

እንደ ኤግዚቢሽኑ ደምብ አንድ እቃ ለገዛ ጎብኚ አንድ ፊርማ ያስገኝለት ነበርና አንድ የፖስት ካርድ በሃምሳ ሳንቲም ገዛሁ። የሰልፉ መንቀራፈፍ ምስጢር ግልጽ የሆነልኝ ተራዬ ሲደርስ ነው። ፊርማቸው ከመደበኛ ፊርማ እጅግ የረዘመ፣ ከስዕል አነስ ያለ ነበር። የሚፈርሙት ደግሞ ቀስ ብለውና በጥንቃቄ ነበር። ከፊርማው በኋላ አርቲስቱ በጋለሪው እየተዘዋወሩ በስዕል ሥራዎቻቸው ላይ ማብራሪያ ሰጡ።

በአፋር ይሁን ሌላ ስፍራ በውል ባይታወሰኝም አንዱ ስዕላቸው የሚያሳየው በድርቅ ምክንያት ሰዎች እሳት እያነደዱ ፈጣሪ ዝናብ እንዲያዘንብላቸው ሲለማመኑ ነበር። የተጥመለመለ ጪስ ትዝ ይለኛል። ቦታው ላይ ክስተቱን ስለተመለከቱት ነበር አርቲስቱ ስዕሉን የሳሉት።

በዩኒቨርሲቲው ቆይታዬ ከከባቢ አየር ሳይንስ ጋር የተያያዙ ኮርሶችን ስወስድ ካገኘሁት ውስን እውቀት ተንተርሼ ሁኔታውን ገመገምኩና በጨዋ ቋንቋ “ማኅበረሰቡ የዋህ ነው” ብዬ አዘንኩ። “እንጨቶቹን ሲያነዱት'ኮ የአየሩን ሙቀት ከፍ ያደርጉታል፤ ይሄ ደግሞ በምድሪቱ የቀረ እንጥፍጣፊ እርጥበት ቢኖር እንኳ ብን ብሎ እንዲጠፋ ያደርገዋል፤ በውጤቱም የውሃ ችግራቸውን ጭራሽ ያባባሱታል እንጂ አይቀንሱትም። ከንቱ ድካም!” ብዬ በውስጤ ከድምዳሜ ደረስኩ።

ጉብኝቱ አበቃ። እኔም ፊርማ ማስፈረም እጅግም ባልተለመደበት ዘመን ያገኘሁትን ብርቅዬ ፊርማ ይዤ ህይወቴን ቀጠልሁ። 

'የጪስን ነገር ጪስ ያነሳዋል' እንዲባል ጉዳዩ ወደ ልጅነት ገጠመኜ ይመልሰኛል። እጅግ ቀደም ብሎ አራተኛ ከፍል ሳለሁ ነው። ክፍለ ጊዜው የሳይንስ ሲሆን መምህራችን በአንዱ ቀን ሊያስተምሩን ሲመጡ ከክፍላቸን ፊትለፊት ከምትገኘው ትንሽ ዛፍ ላይ አንዲት ቅርንጫፍ ቀጥፈው ይዘው ነበር። ጥቂት ቅጠሎች የያዘችውን ቅርንጫፍ እንደያዙ ማስተማራቸውን ቀጥለዋል። ቅጠሎቹ ከእጃቸው እንቅስቃሴ ጋር አንዴ ወደቀኝ፣ አንዴ ወደ ግራ ሲዘናፈሉና እየጠወልጉ ሲሄዱ እመለከት ነበር።

በውል ባላወቅሁት ሁኔታ በሃሳብ ጭልጥ ብዬ ነጎድሁ። ቅጠሎቹ ተመልሰው ህይወት እንደማይኖራቸው፣ እንደሚደርቁ፣ ተጠርገው ከሌላ ቆሻሻ ጋር እንደሚቃጠሉ፣ ጪሱ ደግሞ ወደላይ እንደሚጎን፣ … በመጨረሻም “የጪሱ መድረሻ የት ይሆን?” ብዬ በማሰላሰል ላይ ሳለሁ መምህራቸን “ጥያቄ ያለው!” ሲሉ ከሄድኩበት ተመለስኩ። ከመቅጽበት “ጪስ ወደላይ ሄዶ ሄዶ የት ነው ማረፊያው?” ብዬ ጠየቅሁ። መምህሩ ትዕግስታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ሃይለኛ የሆነ ኩርኩም ካቀመሱኝ በኋላ “እኔ ስለ ተክሎች እያስተማርኩ አንተ ስለ ጪስ ትጠይቀኛለህ”? ብለው ተቆጡ።

ከኩርኩሙ ይልቅ ሃፍረቱ ነበር ያሳመመኝ። 

ከአመታት በፊት ስለ ባህላዊ የዝናብ ማዝነብ ጉዳይ ሳነብ ድርጊቱ በበርካታ አገራት የተለመደ ክንዋኔ ሆኖ አገኘሁት። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ፣ በኢስያ፣ በሰሜንም ሆነ በደቡብ አሜሪካ፣ ወዘተ። በብዙ የአፍሪካ ባህላዊ እምነቶች ምድር የሰዎች ንብረት ሳትሆን ይልቁንስ ምድር ናት ሰዉን የምታስተዳድረውና የምታዘው ብለው ያምናሉ።

ሰዎች ያልተገባ ነገር ሲያደርጉ ምድር ብስጭቷን ከምትገልትጽባቸው መንገዶች አንዱ የዝናብ መጠኗን ቀንሳ ድርቅን በመፍጠር ነው። በዚህም ሳቢያ ሰዎች በዓላትን በማዘጋጀት በጸሎት፣ በዳንስ፣ በመንፈስ፣ በመብላት፣ በመጠጣት፣ ወዘተ የምድርን ብስጭት ለማስረሳትና ይቅርታን ለማግኘት መለማመን አለባቸው። ይህ ንባቤ ቀደም ብሎ በአፋሮቹ ባህላዊ ዝናብ ማዝነብ ስርዓት ላይ የነበረኝን እንቆቅልሽ ከፍ አደረገው። ምክንያቱም ከጸሎት ባሻገር የሚካሄደው የሕብረተሰቡ የዝናብ ማዝነብ ኩነት ከሳይንሱጋ የማይገጥም ስለሚመስል። 

ይባስ ብሎ በኬኒያ ባህላዊ የዝናብ ትንበያዎችን ከዘመናዊው የአየር ንብረት ሳይንስ ጥናት ጋር ለማጣመር መሞከራቸውን አነበብሁ። ከሶስት አመት ቀደም ብሎ “ጸሎተ ዝናብ፡ የኬንያ አገር በቀል ዝናም የማዝነብ ስርዓት” በሚል ርዕስ ኤክዩሜኒካል ሪቪው የተባለ አካዳሚያዊ ጆርናል ላይ በታተመ ጽሁፍ ላይ እንዲህ ይነበባል።

በሚትዮሮሎጂ አገልግሎት የሚደረገው ትንበያ ለሰፋፊ የምድር ክፍሎች የሚያገለግል ስለሆነና የእያንዳንዱን ስፍራ ሁኔታ በዝርዝር ስለማያሳይ፡ የባህላዊ የዝናብ ትንበያዎች ደግሞ በቀበሌ ደረጃ ያተኮረ (finer spatial scale) ዝርዝር መረጃ ስለሚያቀርቡ፡ የሳይንሱ እና የባህላዊው ዝናብ ትንበያዎች ቢቀናጁ የበለጠ ጠቃሚነት አላቸው ይላል።

ምናልባትም ልክ እኛ አገር የሚዘወተሩ የሚትዮሮሎጂ ትንበያ ዜናዎች፤ ለምሳሌ “በአንዳንድ የሃገሪቱ ምሥራቃዊ ከፍታ ቦታዎች መጠነኛ ዝናብ ይኖራል” እንደሚለው አይነት ትንበያ ምርር ተሰኝተው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ወረቀቱ ጥናቱን ሲያጠቃልል የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ በሚደረገው ብሄራዊ ጥረት ውስጥ የባህላዊው የዝናብ ትንበያ መረጃ ግብአት ቢሆን አዋጭ ነው ብሎ አስገነዝቧል። 

ከሶስት አመት በፊት በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2018 አንድ አስገራሚ ዜና ወጣ። እረ እንደውም የቢቢሲ የአማርኛው ቋንቋ ክፍልም ዘግቦት ነበር። “ናይጄሪያዊው የባህል ዝናብ አዝናቢ የሐገሪቱን የአየር ፀባይ መቆጣጠር እችላለሁ አለ” ተባለ።

ግለሰቡ ጎድዊን ኦናሴዱ ይባላል። ምንም እንኳ የናይጄሪያ የሚትዮሮሎጂ ድርጅት “ቅዠታም” ቢለውም ጎድዊን የማዝነብ ክህሎቴን ያገኘሁት ከዘር በተዋረድ ተላልፎ የወረስኩት ችሎታዬ ነው ይላል። ይህን ጉዳይ ለማጣራት ፒድጊን የተባለ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጎድዊን ኦናሴዱ ከሚገኝበት የደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ ኢፍቴዱኑ ቀበሌ ድረስ ተጓዘ። ወቅቱ የዝናብ ቢሆንም ጋዜጠኛው ስፍራው ከመድረሱ በፊት የአየሩን ሁኔታን ከጉግል ትንበያ ላይ ተመልክቷል።

በዕለቱ ዝናብ እንደማይዘንብ ተረድቷል። እርግጥም እዚያ ሲደርስ እለቱ ጸሃያማ ነበር። እንደተገናኙ ጎድዊን ለጋዜጠኛው “አንዳንድ ሰዎች የቀብር ስነስርአት ሲኖርባቸው ዝናቡን እንዳስቆምላቸው ይጠይቁኛል … ነገር ግን አንተ የመጣኸው የእኔን ችሎታ ለመፈተን ስለሆነ ዛሬ ዝናብ አዝንቤ አሳይሃለሁ” አለው። ቀጥሎም በጎድዊን ጥያቄ መሰረት ሁለት ሳጥን ቢራ፣ አንድ ጠርሙስ አረቄ፣ 1000 ኒያራ (ወደ ሁለት ዶላር ገደማ መሆኑ ነው)፣ ሻማዎች፣ ጨርቆች፣ ወዘተ ተሟልተው ቀረቡለት።

ጎድዊን ከቤቱ አቅራቢያ እንጨትና ቅጠላ ቅጠሎችን አቃጠለ። ለጋዜጠኛው ሲያስረዳ እሳቱ የዝናብ ማዝነብ ሂደት አንዱ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ፣ እሳቱ እየነደደ ሳለ ዝናቡ መዝነብ እንደማይጀምር፣ ነገር ግን እሳቱ ከጠፋ በኋላ በስነስርአቱ ሂደት ወቅት ዝናብ ይዘንባል አለ። 

እሳቱ እንዲጠፋ ከተደረገ በኋላ ከመኖሪያ ቤቱ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው የዝናብ ማዝነቢያው ማማ ዘንድ ተጓዙ። ጋዜጠኞቹና ያካባቢው ሰዎች በታደሙበት ስፍራ ጎድዊን ነጭ ልብሱን ለብሶ ተከሰተ። የማዝነቢያ ማማው በሁለት ረዣዥም ዛፎች መሃል ነው። ጎድዊን በጎላ ድምጽ መነባነብ ጀመረ። የዝናብ ጠብታ አልታየም። የህዝቡም ሆነ የካሜራው አይኖች ስራቸውን እንደቀጠሉ ነበር።

መነባነቡ ለ45 ደቂቃ ሳይቋረጥ ቢቀጥልም ዝናቡ ግን ወይ ፍንክች! ትይንቱን ሲመለከት የነበረው ሰዉም ተሰላቸ መሰል ስፍራውን ጥሎ ወደየቤቱ መሄድ ጀመረ። ጎድዊን ድንገት መነባነቡን አቋርጦ “እስኪ ወደ ቤቴ አካባቢ ሂድና ሁኔታውን አጣራ” ብሎ ረዳቱን ላከው። ረዳቱ ከተላከበት ቤት ደርሶ ሲመለስ አንድ ለጎድዊን ጥሩ ያልሆነ ስሜት የነበረውና የአእምሮ ህመም ያለበት ግለሰብ ቀድሞ አጥፍተውት የነበረውን ቀሪ እንጨት በድጋሚ ለኩሶ እሳቱን እያነደደ እንደነበረ ተናገረ።

ጎድዊን ተበሳጭቶ የቀረውን ህዝብና ጋዜጠኞቹን ትቶ ወደ ቤቱ ለመሄድ ሲሰናዳ ሪፖርተሮቹ “ለተጨማሪ ሁለት ሰዓታት ብቻ እንታገሳለን” ብለውት እዚያው ቆዩ። ሆኖም ግን ልክ ለአንድ ሰአት ተኩል ያህል ጊዜ እንደጠበቁ ሪፖርተሮቹም ተስፋ ቆርጠው እቃዎቻቸውን መቀርቀብ ጀመሩ። ይህን ጊዜ የቅዝቃዜ አየር በዝግታ መንፈስ ጀመረ። የዛፍ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች በንፋሱ ሳቢያ መውለብለብ ጀመሩ።

የጋዜጠኞቹ አይኖች ወደሰማይ አንጋጠጡ። ደመናውም ዝናብ እንዳረገዘና መዝነቡ አይቀሬ መሆኑን ተገነዝበው በፍጥነት የመቅረጫ መሳሪዎቻቸውን ከየኮሮጆዎቻቸው አውጥተው ለቀረጻ አዘጋጇቸው። ከባድ ባይባልም ዝናብ ዘንቦ መሬቱን በመጠኑ አረጠበው። በመጨረሻም ሪፖርተሩ ሁኔታውን ሲዘግብ “ሰዎች የጎድዊንን ችሎታ ሊያምኑ ወይንም ሊጠራጠሩ ይችላሉ። እኔ ግን በዕለቱ መዝነቡን እመሰክራለሁ፤ ሆኖም ግን ዝናቡ የዘነበው በተፈጥሮ ይሁን በጎድዊን ሳቢያ መለየት አልችልም” አለ።

በኢትዮጵያስ የባህላዊ የዝናብ ማዝነብ የጽሁፍ መረጃ ይኖር ይሆን ብዬ ትንሽ ፍተሻ ሳደርግ በቅድሚያ ያገኘሁት ደስታ ወ/መስቀል በ2006 ለድህረ ምረቃ የስነጽሁፍ ፎክሎር ዘርፍ የምረቃ ማሟያ “የዲዚ ብሔረሰብ የለቅሶ ስርዓተ ክዋኔ” በሚል ርዕስ ያቀረቡትን ጽሁፍ ነው።

በደቡብ ክልል ማጂ ወረዳ ውስጥ የሚገኙት የዲዚ የጎሳ መሪዎች (ባላባቶች) የሀይማኖትም በኩል መሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ በተፈጥሮም ላይ ስልጣን እንዳላቸው እንደሚታመን፣ የዝናብ እጥረት ሲኖር ዝናብ እንደሚያዘንቡ፣ ዝናብ ሲበዛ (ወይንም ያለወቅት ሲዘንብ) ደግሞ ዝናቡን ማስቆም እንደሚችሉ፣ ወዘተ ያትታል። 

ሌላው ደግሞ “የሲዳማ ዝናብ ማዝነብ በዓል” ነው። የተጻፈው በዶና ሲለን፣ የተገኘው ደግሞ ከ https://commonriver.org ድረ ገጽ ነው። እንደ ዘገባው በ2002 በደቡብ ኢትዮጵያ አለታ ወንዶ አካባቢ ይጠበቅ የነበረው የክረምቱ ዝናብ ቀረ። ህዝቡ “ቀጣዩ ዝናብ መች ይሆን የሚመጣው?”፣ “አዝመራው መልሶ ያገግም ይሆን”?፣ “ለቀጣዩ አመት የሚላስ የሚቀመስ ይገኝ ይሆን?”፣ “የቡና ዛፎቹስ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆን”?፣ ወዘተ እያለ ተጨነቀ።

ለዚህ ሁሉ እንቆቅልሽ መፍትሄው በባህላዊ መንገድ ዝናብ ማስገኘት ነበር። አባቶች አመቺውን ቀን ወስነው ዝግጅቱ ተጀመረ። ለእርድ የሚሆን በሬ ተዘጋጀ። በዕለቱ የጎሳ መሪዎች በባህላዊ ልብሶቻቸው ደምቀው ቀረቡ። የበዓሉ ተሳታፊዎችም በከተማው ከሚገኝ የእድሜ ጠገብ ዛፍ ስር ተቀመጡ። ዝግጅቱ በጸሎት ተጀመረ። በሬው ከታረደ በኋላ ደሙ በሰዉ ግንባርና ደረት ላይ ተቀባ። ስጋው ተጠብሶ በእንሰት ኮባ ላይ እየተደረገ ለታዳሚው ቀረበ።

የበሬው ሆድ እቃ ለአዛውንቱ እይታና ትርጉም ትንተና ቀረበ። በውጤቱም ዝናቡ በፍጥነት ዘንቦ ተክሉን በመታደግ ቀጣዩ አመት ጥጋብ እንደሚሆን ተተነበየ። ጥቂት ሰዎች የትንቢቱን ውጤት ለማየት ቆይተው ጠበቁ። ለእኩለ ለሊት ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀረው ሃይለኛ ዝናብ ዘነበ። ከሁለት አመታት በኋላ በ2004 በድጋሚ የዝናብ እጥረት ተከስቶ ነበር። ባህላዊው የዝናብ ማዝነብ ስርዓት ተከናውኖ ውጤቱም ተመሳሳይ እንደነበር ተዘግቧል። አላገኘኋቸውም እንጂ በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተዳሰሱ መረጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገምታለሁ። 

ሁለት ጥያቄዎች ፈተኑኝ።

እንዴት ነው በጣም ተራርቀው ሳለ ሳይኮራረጁ የተለያዩ ባህሎች ይህንን የዝናብ ማዝነብ ችሎታ ያስመሰከሩት?

በሳይንሱና የባህላዊው የማዝነብ ሂደት መሃል ያለው ከፍተኛ ልዩነት እንዴትስ ይታረቃል? በቀጣይም የሚከተለውን ነገር ልብ አልኩ።

በአፋርም ይሁን በኬንያ፤ ናይጄሪያ በሚገኘው ኢፍቴዱኑም ይሁን በማጂ ወይንም በአለታ ወንዶ የሚወራረሱ የጋራ ባህሪያትን ለየሁ። የቦታ (ከቤት ውጪ መከናወናቸው)፤ የጊዜ (በዝናብ ወቅት መሆኑ)፤ የድርጊት (እንጨት ወይንም ጭራሮ የማንደድ) መመሳሰልን። በተጨማሪም እንደየ አካባቢው ባሕልና እምነት ስነስርአቱን የሚያጅቡበት የዳንስ፤ የአምልኮ፤ ወዘተ ባህሪ ይኖራቸዋል። 

በተለያየ ጊዜ እዚህም እዚያም ያገኘኋቸውን መረጃዎችን ሳጠናቅር የደረስኩበት ምስል እንደሚከተለው ነው።

ደመና እንዲፈጠር ሁለት አበይት ነገሮች ሊሟሉ ይገባል።

1ኛ/ የአየሩ መቀዝቀዝና

2ኛ/ የደመና አስኳል (cloud condensation nuclei) መፈጠር።

የተፈጥሮ ዝናብ አፈጣጠር በርካታ መንገዶች ሲኖሩት ሁሉም መንገዶች የሚጋሩት አንድ ጉዳይ አለ፤ አየር ወደላይ ተገፍቶ የመውጣቱ (atmospheric lifting) ጉዳይ። አየር ተገፍቶ ወደላይ በሚወጣ ጊዜ የሙቀት መጠኑ እየወረደ ይሄድና አንደኛው የደመና ምስረታ ቅድመ ሁኔታ ይሟላል። ሆኖም ወደላይ የተገፋ አየር ሁሉ ዝናብ አያመጣም። የደመና አስኳልም ያስፈልጋል። አስኳሉ የሚፈጠረው በጣም ጥቃቅን (microscopic) ብናኝ ከሆኑ ነገሮች፡ ማለትም አቧራ፣ የእንጨትም ሆነ የተሽከርካሪ ጪስ፣ የውሃ ጠብታ፣ የአበባ ብናኝ፣ የባህር ጨው፣ ባክቴሪያ፣ ወዘተ ነው።

እነኚህ ብናኞች ልክ እንደ ማግኔት ሆነው በዙሪያቸው የሚገኙትን ተኖች በመሳብ ወደ ደመና ነጠብጣብነት ወይንም በረዶነት ይቀይሯቸዋል። በሌላ አባባል ፍጹም ንጹህ የሆነ የከባቢ አየር ደመና እንዲከማች ወይንም ዝናብ እንዲፈጠር አያስችልም ማለት ነው። አሁን በኢትዮጵያ የተከናወነው ቴክኖሎጂ የተገኘው ሳይንቲስቶች ተፈጥሯዊውን የደመና አስኳል ማጎልበት ሂደት በሰው ሰራሽ መንገድ የማፍጠኛ ብልሃት ስላበጁለት ነው።

በአውሮፕላንም ይሁን በሌላ ዘዴ ሆን ብሎ ብናኝ ኬሚካሎችን (ለምሳሌ silver iodide) በደመና ላይ በመዝራት የደመናውን አስኳል አዳብሮ ዝናብን ማዝነብ ተቻለ ማለት ነው። እኔም ለረዥም ጊዜ ከዝርዝሩ መሃል ተካቶ የነበረውን ጭስ ቁብ ሳልሰጠው ቆይቼ ኖሯል።

በተፈጥሯዊና የባህላዊ ዝናብ አፈጣጠር መሃል ያለው የጋራ ባህሪ ደግሞ ይህ ይመስለኛል። ሁለቱም መንገዶች ለደመና አስኳል መፈጠር ሚና ካላቸው ብናኞች አንዱ በሆነው በጪስ ይገናኛሉ። ከላይ እንደተጠቀሰው በባህላዊ መንገድ የሚፈጥሩ ዝናቦች በክረምት ወራት ከቤት ውጪ ሆኖ እሳት እየነደደ የሚከናወን ስርዓት ነው። ጪሱ ወደ ላይ ሄዶ በደመና ግንባታና ዝናብ ማዝነብ ሂደት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል።

እነሆ ጥቂት ምሳሌዎች።

ትላልቅ እሳተ ገሞራዎች ሲፈጠሩ ብዙውን ጊዜ ሃይለኛ ዝናብ ይከተላል። ምክንያቱም ከፍተኛ ክምችት ያለው አመድ፣ ጋዝና፣ ጭስ አብሮ ወደሰማይ ስለሚወነጨፍ ነው።

ሌላም አለ።

ጥርት ብሎ የነበረ ሰማይ ላይ አውሮፕላኖች እንዳለፉ ረዣዥም ነጭ መስመርች ይፈጠራሉ። ሲታዩ መጠናቸው ይነስ እንጂ ደመናዎች ናቸው የተፈጠሩት። ይህም የሚሆነው ከአውሮፕላኑ የሚወጣው ጭስ የደመና አስኳሉ እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ነው። በአየሩ ውስጥ በቂ እርጥበት ባይኖር ይህ ደመና ሊፈጠር አይችልም። ይህ ማለት ግን ዝናብን ፍለጋ ዝም ብለን እሳት እንድናነድ መገፋፋቴ አይደለም። ለሲጋራ አጫሾችም አጉል የማጨሻ ሰበብ ለማቀበልም አይደለም።

የማዝነብ ሂደት እንዲሳካ ቀድሞውኑ አንድ ላይ ሊሰባሰብ ያልቻለ በቂ እርጥበት በአየሩ ውስጥ ሊኖር ይገባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በደረቅ ወራት ወቅት እሳት ቢነድ ጪሱ የሚያስከትለው የባሰ ድርቀትን ነው። ይህ ጉዳይ ደግሞ በናሳ ሳይንቲስቶችም የምዕራብ አፍሪካን አጥንተው ያረጋገጡት ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው ከላይ “በክረምት ወቅት” የሚል ነገር የጠቆምኩት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በርካታ የደመራ በዓላት ምሽቶችን የዝናብ ሁኔታ ሳልከታተል መኖሬ ይቆጨኛል። 

እጅግ ቆይቶም ቢሆን በስተመጨረሻው ለመምህራቸን አቅርቤው ለነበረ የድሮ ጥያቄዬም ምላሽ አገኘሁለት። በመላው አለም ተሰራጭተው ከትውልድ ትውልድ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ባህላዊ ዝናብ አዝናቢዎች ምናልባትም ቢጠየቁ የጪሱን ግልጋሎት በትክክል ላይገልጹት ይችላሉ። ማን ያውቃል፡ ከጪሱ በተጨማሪ ሌላ የዝናብ ማዝነቢያ ምስጢርም ሊኖር ይችላል።

ሆኖም ግን ከበርካታ ዓመታት በፊት “የዋህ ማኅበረሰብ” ብዬ አዝኜላቸው የነበሩትን የአፋር የባህል ዝናብ ተለማማኞችን ይቅርታ ከጠየቅሁ ጥቂት የማይባል አመታት ተቆጠሩ።

የሆነው ሆኖ በየዘርፉና በየቦታው ስንት ያልተጠና የአገር በቀል የማኅበረሰብ እውቅት ይኖር ይሆን? መንደር ይቁጠረው።

 


Share

Published

By Daniel Kassahun (PhD)

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service