የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ታላቁን የጀርመን-አፍሪካ 2021 ሽልማት ተሸለሙ

*** የጀርመን-አፍሪካ ፋውንዴሽን ዶ/ር ዳንኤል “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥና ገለልተኝነቱ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንዲሰፋ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና እውቅና የሚሰጥ” ነው ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Cpmmission.

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Cpmmission. Source: D.Bekele

ኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ታላቁን የጀርመን-አፍሪካ 2021 ሽልማት በመሸለማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገለጡ።

የጀርመን-አፍሪካ ፋውንዴሽን (DAS) ዛሬ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የሽልማቱን እጩዎችን የሚያወዳድረው ኮሚቴ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ለዚህ በጀርመን አገር በአይነቱ ከፍተኛ ለሆነው ሽልማት ሲመርጣቸው በሙሉ ድምጽ እንደሆነና፣ ሽልማቱ ዋና ኮሚሽነሩ “በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲሰፍን ለሚደረገው ጥረት ላበረከቱት የሕይወት ዘመን አስተዋጽዖ” እውቅና የሚሰጥ እንደሆነ አሳውቋል።

በተጨማሪም፣ የፋውንዴሽኑ መግለጫ ሽልማቱ ዶ/ር ዳንኤል “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በከፍተኛ ደረጃ እንዲለወጥና ገለልተኝነቱ እንዲረጋገጥ፣ እንዲሁም ሥልጣንና ኃላፊነቱ እንዲሰፋ ለተጫወቱት ቁልፍ ሚና እውቅና የሚሰጥ” መሆኑን አክሎ ገልጿል። ይፋዊ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በእ.ኤ.አ. ኅዳር 2021 የሚካሄድ ይሆናል።

ከ25 ዓመታት በላይ በየዓመቱ ሲካሄድ የቆየው ይህ ሽልማት፣ በሙያቸው የላቀ አመራር ላሳዩና ለእድገትና ለመሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አፍሪካውያን የሚሰጥ ነው። ከዚህ ቀደም ሽልማቱ ከተበረከተላቸው አፍሪካውያን መካከል የቀድሞው የማሊ ፕሬዝዳንት አልፋ ኡማር ኮናሬ፣ የጋናው የሕግ ባለሞያና ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሃመድ ኢብን ቻምባስ እንዲሁም የኬንያው የፀረ-ሙስና ተሟጋች ጆን ጊቶንጎ ይገኙበታል።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ይህንን ክብር ለማግኘት የበቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው።

ለጀርመን-አፍሪካ ሽልማት የታጩ እጩዎችን የሚያወዳድረው ኮሚቴ ከጀርመን ፌዴራል የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ ከፌዴራል የኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ሚኒስቴር በተውጣጡ ባለሙያዎችና ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ ፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ተወካዮች እና ከሌሎች የአገሪቱ ታዋቂ ሰዎች የተዋቀረ ነው።

ኮሚቴው የሚያወዳድራቸው የእጩዎች ዝርዝር በአፍሪካ በተወከሉ ወይም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት ባሏቸው የግል ድርጅቶችና ሌሎች ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአህጉሩ በሚገኙ የጀርመን ኤምባሲዎች በሚላኩ ጥቆማዎች መነሻነት የሚዘጋጅ ነው።

ሽልማቱን አስመልክቶ የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ “ዶ/ር ዳንኤል ‘ማየት የምትሹትን ለውጥ ሁናችሁ ተገኙ' የሚለውን የእንግሊዘኛ ብሂል ማሳያ ስለመሆናቸው ሁላችንም የኢሰመኮ ሰራተኞች የምንመሰክረው ነው” ያሉ ሲሆን፣ አክለውም “የዳንኤል በር ለማንኛውም እሱን ለሚፈልግ ሰው ዝግ ሆኖ አያውቅም፣ ከባልደረቦቹ ሁለት እጥፍ የሚተጋና የሰዎችን እምቅ አቅም ጭምር የመለየት አቻ የሌለው ችሎታ ያለው ሰው ነው። ዋና ኮሚሽነራችን ላገኙት እውቅና ሙሉ ድጋፋችንን ስንለግስ በከፍተኛ ኩራት ነው” ብለዋል።


2 min read

Published

By Stringer Report


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now