የባልደራስ-መኢአድ የጋራው ምክር ቤት በ09/01/2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የቅንጅቱን ፕሬዚዳንት ፣ ም/ል ፕሬዚዳንት እና ሥራ አስፈፃሚውን በሙሉ ድምፅ መርጧል፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ መስከረም 12/01/2013 ይፋ ባደረገው ጋዜጣዊ መግለጫው "በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሶስት አስርት ዓመታት በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ አቶ እስክንድር ነጋ አድልዎንና ኢፍትሃዊነትን በብዕራቸው በመታገል የሚታወቁት ናቸው። ነገር ግን ዛሬም እንደገና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ይህ ውንጀላና እስር በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንደሆነ የሚያምነው የባልደራስ -መኢአድ ከፍተኛው ምክር ቤት ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ ክቡር አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ሆነውም ቢሆን የባልደራስ-መኢአድ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ እኚህን የህዝብ ልጅና መሪ መንግስት በፍጥነት ከእስር እንዲለቅም ምክር ቤቱ በጽኑ አሳስቧል" ሲል የአቶ እስክንድርን በእሥር እያሉ በፕሬዚደንትነት መመረጥ አስታውቋል።
አያይዞም "ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸውና በተደጋጋሚ ለእስር የተዳርጉትን የነፃነት ታጋዩን አቶ ማሙሸት አማረን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን አቶ ማሙሸት አማረ ለህግ የበላይነት ለዴሞከራሲ ስርአት ግንባታ የከፈሉትን ወደር የሌለው መስዋእትነትና ቁርጠኝነት የቅንጅቱ ምክር ቤት ያደነቀ ሲሆን በቀጣይነት ትግሉን በመምራት ቅንጅቱ በአሸናፊነት እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ምክር ቤቱ እምነቱን ገልጿል" በማለት የምርጫ ውጤቱን ገልጧል።
በቀጣይነትም፤
- ምክር ቤቱ ለሌሎች ፓርቲዎችም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ከባልደራስ መኢአድ ጋር አብሮ ለመስራት የጠየቁትን ፓርቲዎች በቅርቡ አብሮ ለመስራት የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚጀምር የገለጸ ሲሆን ሌሎች ከቅንጅቱ ጋር ለመስራት ፍላጎት ያላቸውን ፓርቲዎች የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ቅንጅቱን እንዲበቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል
- በቅርቡ በቤንሻንጉል ክልል በንጹሃን አርሶ አደር ወገኖቻችን ላይ ማንነትን መሰረት ባደረገው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልጻለን
- ምክር ቤቱ ይህንን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ እያወገዝ መንግስት ሙሉ ሃላፊንቱን እንዲወስድ
- በወለጋ፣ በሚዛን ቴፒ፣ በሐረር፣ በደራና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁ ቡድኖች አማካኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ሲሆን በቀጣይም አስከፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የመከላከል ርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክር ቤቱ ያሳስባል
- በጎርፍ መጥለቅለቅ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም በመተሃራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እንዲሁም በጣና ዙሪያ ባሉ ጉማራና ርብ ወንዞች መሙላት በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ህይወታቸውንና ንብረታቸው ላጡ ወገኖቻችንም ከልብ ማዘናችንን እንገልጻለን
- ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ / Coved 19 / ወደ ሀገራች መግባቱን ተከትሎ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት መላው ህዝባችን ሳይዘናጋ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል
- የሀገራችንን ኢትዮጵያ መፃዒ እጣፈንታ የተሻለ ለማድረግ በምናደርገው ወሳኝ ትግል ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የምትኖሩ የቅንጅቱ ደጋፊዎች የሚጠበቅባችሁን ትግል እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን ብሏል።
የመላው ኢትዮጽያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ /የካቲት 29 /2012 ዓ.ም በመኢአድ ጽህፈት ቤት ባደረጉት ስብሰባ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንጅት ለመስራት ያደረጉትን ስምምነት ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል ፡፡