የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ) ዛሬ በተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ እስከ እኩለ ቀን የተደረገውን የምልከታ ሥራ የሚያሳይ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
ኅብረቱ ከ3,000 በላይ ታዛቢዎችን በመላ አገሪቱ በሚገኙ 2,258 የምርጫ ጣቢያዎች በማሰማራት የምርጫውን ሂደት ሲከታተል መቆየቱን ገልጿል።
በሪፖርቱ መሠረት፣ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጠት ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ መጀመሩ ተመዝግቧል። ከተሰማሩት ታዛቢዎች 99 በመቶ የሚሆኑት ያለምንም ገደብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመግባት የትዝብት ሥራቸውን ማከናወን ችለዋል ተብሏል።
ኅብረቱ በምርጫው አፈፃፀም ውስጥ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እየተበረታታ መሆኑንም ጠቁሟል። በ61 በመቶ የሚሆኑ ጣቢያዎች ከአንድ በላይ ሴት አስፈፃሚዎች የተመደቡ ሲሆን፣ በ26 በመቶ ጣቢያዎች ደግሞ ሴቶች የአመራር ኃላፊነት ይዘው ሲያገለግሉ መታየታቸውን አስታውቋል።
ሆኖም በምርጫው ሂደት ላይ በርካታ አሳሳቢ ግድፈቶችና የፀጥታ ችግሮች መታየታቸውን ኅብረቱ ገልጿል።
በአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አምባ ጊዮርጊስ፣ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ እና ደብረ ታቦር አካባቢዎች የተኩስ ድምፅ በመሰማቱ ምክንያት የምርጫ ሂደቱ ለጊዜው መቋረጡን አስታውቋል።
በአንዳንድ ጣቢያዎችም አስፈፃሚዎች ጣቢያዎችን ዘግተው ለመውጣት መገደዳቸው መመዝገቡን ገልጿል።
በአዲስ አበባና በሀዋሳ በሚገኙ አንዳንድ ጣቢያዎች የብልፅግና ፓርቲ ወኪሎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ መታየታቸውን ኅብረቱ ገልጿል።
በተጨማሪም በሀዋሳ ቱላ ወረዳ የቀበሌ አመራሮች እስከ ድምፅ መስጫ ሳጥን ድረስ በመሄድ መራጮች ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድሩ መታዘባቸውን በሪፖርቱ አመልክቷል።
ከሥነ-ሥርዓት ግድፈቶች መካከል ማኅተም ያልተደረገባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መሰራጨታቸው፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች ባዶ መሆናቸው ሳይረጋገጥ መታሸጋቸው እና ታዛቢዎች ወደ ጣቢያዎች እንዳይገቡ የመከልከል ሁኔታዎች በአንዳንድ ቦታዎች መከሰታቸውን ጠቅሷል።
በተጨማሪም አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በጤና ተቋማትና በሆስፒታሎች ግቢ ውስጥ መቋቋማቸው መታየቱን ገልጿል። ኅብረቱ እንደሚለው ይህ ሁኔታ በምርጫ ሕጉ የተከለከለ ቢሆንም በተግባር ተፈጽሞ ታይቷል።
ኅብረት ለምርጫ እስከ እኩለ ቀን ድረስ 203 አሳሳቢ ክስተቶችን መቀበሉን ገልጾ፣ ከእነዚህ ውስጥ 40 ጉዳዮች መረጋገጣቸውን እና ቀሪዎቹ 163 ጉዳዮች አሁንም በማጣራት ሂደት ላይ መገኘታቸውን አስታውቋል።
ኅብረቱ በመጨረሻ ዝርዝር ግኝቶችን የያዘ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ምርጫ ቦርድ ወቅታዊ መግለጫዎችን በተከታታይ እንደሚሰጥ ያስታወቀ ሲሆን፤ የመጨረሻ ውጤቶችን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 2 ይፋ እንደሚደረጉም አስታውቋል።

