በኢትዮጵያ ለ60 ዓመታት ሥራ ላይ የነበረው የንግድ ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ

*** ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በኢትዮጵያና በኡጋንዳ መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠትና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የፍትሕ ትብብር ስምምነትንም አጽድቋል።

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

በኢትዮጵያ ለ60 ዓመታት  ስራ ላይ የነበረውን የንግድ ህግ  አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን  ረቂቅ አዋጅ የህዝብ ተወካዮች  ምክር  ቤት አጸደቀ።

የንግድ ህጉን ማሻሻያ በዛሬው እለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሙሉ ድምጽ አፅድቆታል።

በምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ መሰረት አባተ የንግድ ህጉን ረቂቅ አዋጅ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

በዚሁ ጊዜ ባለፉት 34 ዓመታት የንግድ ህጉን ለማሻሻል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢደረጉም ማሻሻያው ለምክር ቤቱ የቀረበው በመስከረም ወር 2013 ዓ.ም መሆኑን አስታውሰዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ረቂቅ አዋጁን የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በዝርዝር አይቶ ማሻሻያ ማድረጉንም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የንግድ እንቅስቃሴ አኳያ ለነጋዴው የተሳለጠ አሰራር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ሰብሳቢዋ፣ በተለይ አገሪቷ የአለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ያሳልጣል ብለዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የህጉ መሻሻል በተለይ በንግዱ ዘርፍ የሚታዩ ህገወጥ አሰራሮችን ለማሻሻልና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት ለመዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በኢትዮጵያና በኡጋንዳ መካከል የተደረገውን በወንጀል ጉዳዮች የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ መስጠትና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነትንም አጽድቋል።

ስምምነቱ ወንጀል ፈጽመው ከአገር የሚሸሹ ሰዎችን ለፍርድ ለማቅረብና በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

በሌላ በኩል ኢትዮጰያና ኡጋንዳ ያላቸውን የድንበር ዘለል ወንጀል ተጋላጭነት በዘመናዊ የምርመራ ዘዴ መረጃና ማስረጃዎች ሳይጠፉ ምርመራ በማከናወን በፍርድ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያደርጋል ተብሏል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባ የጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱን ኢዜአ  ዘግቧል።


2 min read

Published

By Stringer Report


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now