የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት የመጨረሻ ምዕራፍ ያለውን መቐለ ከተማ የሚገኙትን የሕወሓት አመራርና ተዋጊ አባላትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ ሥፍራዎችን መያዙን በመከላከያ ሠራዊት ኅብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሂም ለአገር ውስጥ ብዙኅን መገናኛ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በመግለጫቸውም በአድዋ ግንባር የተንቀሳቀሰው ሠራዊት ሃውዜን፣ አብርሃ ወአፅብሃንና ውቅሮንና አጉላን እንዲሁም አል ነጃሺ፣ አዲቀየህና ማይመሳኖ በቁጥጥር ስር ማዋሉን፤
በሁለተኛው የአዲግራት ግንባር በኩል ሳንቀጣና አልነጃሺን ተቆጣጥሮ ውቅሮ መግባቱንና በሶስተኛው የራያ ግንባር አዲቀይህንና ሂዋናን መያዙን ገልጠዋል።
ሠራዊቱ በመቐለ አቅራቢያ ወደሚገኘው መሰቦ ተራራ እያመራ ሲሆን ይህም መቐለን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመቆጣጠር ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል።
በሕወሓት አመራር በኩል ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መቐለ "የቦምብ ጥቃት" እየደረሰባት መሆኑን ለሮይተርስ የገለጡ ሲሆን ከቀናት በፊት የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከአፍሪካ ሕብረትና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አባላት ጋር አስቸኳይ ተኩስ አቁም በማድረግ የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ እየተነጋገሩ ያሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ አንዳለም፤ በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአፍሪካ ህብረት ልዑክ ቡድ አባላት የሆኑትንና በየቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ዮኣኪም ቺሳኖ የሚመሩትን የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍንና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኪጋሌማ ሞትላንቴ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

