ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዳር 19 - 2013 በትግራይ የተካሄደው ዘመቻ መጠናቀቁን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በትግራይ ክልል ስናካሂድ የነበረው የሕግ የማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁንና መቆሙን ላሳውቅ እወዳለሁ። በዚህ ዘመቻችን ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል” ብለዋል።
ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴም በበኩላቸው “ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ የመከላከያ ኃይላችን ላጎናጸፈን ክብር መላው ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን”
“ሕግ የማስከበሩ ምዕራፍ በድል ተጠናቋል፤ በመጭው ጊዜ ደግሞ ትልቅ ሥራ እንደሚጠብቀን ለአፍታም አንዘናጋ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላፈዋል።
የአገር መከላከያ ኃይል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላም በሰጡት መግለጫ የመከላከያ ሠራዊቱ "የአገር መከላከያ ሠራዊት በትናንትናው ዕለት የመቐለ ከተማ ነዋሪ ላይ ጉዳት ሳይደርስ እንዴት ከተማዋን መቆጣጠር ይቻላል በሚለው ላይ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን" ጠቁመው "ይህንን ተከትሎም በዛሬው ዕለት ከሰዓት ላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል" ሲሉ ገልጠዋል።
አያይዘውም "ሰባት ሺ የሰሜን ዕዝ አባላትን ነፃ ማውጣቱን፣ ታንኮች፣ መድፎች፣ ብረት ለበሶችና ከባድ መሣሪያዎች፣ ዴፖዎች በሠራዊቱ ቁጥጥር ስር መዋሉን" አንስተው "ሠራዊቱ መንግሥት የሰጠውን የመጨረሻውን ምዕራፍ ዛሬ አጠናቅቋል። በቀጣይ እከሌ የሚባል በቁጥትር ስር ዋለ እያልን ለሕዝባችን እያሳወቅን እንሄዳለን " ብለዋል።
በሕወሓት አመራር በኩል ሮይተርስ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጦራቸው ከመቀሌ አካባቢ መልቀቁን ጠቁመው ሆኖም በፍልሚያው እንደሚቀጥሉ የገለጡለት መሆኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን በበኩሉ ከ43,000 በላይ ከትግራይ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ስደተኞች መኖራቸውንና መሠረታዊ እገዛዎችን እያደረገ መሆኑን ገልጧል።
የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በውጊያው የተፈናቀሉትን ሰዎች ለመርዳት የሱዳን መንግሥት 200 ሚሊየን የአውስትራሊያ ዶላርስ እንደሚያሻው ተናግረዋል።
አያይዘውም "የሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተመልክተናል። ሆኖም በቀን ከአምስት እስከ ስድስት መቶ የተፈናቃዮች ቁጥር ትንሽ የሚባል አይደለም" ብለዋል።

