በፌዴራልና ትግራይ ክልል መንግሥታት መካከል ተቀስቅሶ ያለውን ጦርነት አስመልክቶ ወደ ድርድር እንዲገባ ዓለም አቀፍ ጫናዎች ቢከተሉም በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት በኩል ግና 'እየወሰድን ያለነው እርምጃ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር ስለሆነ ወደ ድርድር የሚያስኬደን ምክንያት የለም' በሚል በወታደራዊ ኃይል እርምጃው ገፍቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረ ኃይል የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በሰጡት መግለጫ "ዘመቻው የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ብቻ" እንደሆነ በመጥቀስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ "የጊዜ ስጡን" መልዕክት አስተላልፈዋል።
"የኢትዮጵያ ባለ ስልጣናት ከሕወሓት ጋር በዑጋንዳ አሸማጋይነት የሽምግልና ውይይት ላይ ሊሳተፉ ነው" ተብሎ በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች የተገለጠው "የተሳሳተ ዘገባ" እንደሆነና "የዑጋንዳውን ፕሬዚደንት ሙሴቪኒንም ሆነ ሌላ አገር እንዲያደራድሩን አልጠየቅንም" ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ግና ከፌዴራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር በውጊያ ላይ ያለው የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ እንዲገባና ልዩነቶችም በድርድር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የዜና አውታሩ ሮይተርስ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሰኞ ዕለት መቐለ ላይ የቦምብ ጥቃት ማድረሱን ከዲፕሎማቶችና ወታደራዊ ምንጮቼ አገኘሁት ያለውን መረጃ እንዲያረጋግጡለት ለሕወሓት መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በቴክስት ላቀረበው ጥያቄ "ሁለት ያህል ሰዎች ተገድለዋል። አንድ ቆስሏል። መቐለ ላይ ቦምብ እየተጣለ ሳለ አላማጣም በድሮን ጥቃት ደርሶባታል" ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጧል።
ሮይተርስ በወቅቱም ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምላሽ አለማግኘቱንና ሆኖም አላማጣ በፌዴራል መንግሥት ወታደሮች ከሕወሓት እጅ መውጣቷ እንደተነገረ ጠቅሷል።

