በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እጅግ ርካሽ በሆነ ዋጋ ኮርሶችን ሊሰጡ ነው

** በመቶዎች የሚቆጠሩ የደቡብ አውስትራሊያ ጤና ሠራተኞች በክትባት ሙከራ ሊሳተፉ ነው

Core Bulletin - 12/04/2020

online learning Source: Supplied

 

ቫይረስ ትምህርት

 ከወርኃ ሜይ ጀምሮ ተከስተው ያሉትን የሙያ እጥረቶች ለመሸፈን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የኮሮናቫይረስ ቀውስ እስኪያበቃ እጅግ በረከሰ ዋጋ ኮርሶችን ይሰጣሉ። 

 ሂደቱ አያሌ የሥራ አጥነትን ተከትሎ አዲስ የሙያ ክህሎት የሚሹ ሰዎችን ለብቃት ያደርሳል።  

 የትምህርት ሚኒስትር ዳን ቲሃን የኮርስ ክፍያዎቹ ዋጋ ከ 50 ፐርሰንት እስከ 74 ፐርሰንት ዝቅ እንደሚል አስታውቀዋል።

 ለስድስት ወራት የሚሰጡት ኮርሶች የሚያተኩሩት ለአገሪቱ አስፈላጊ ከሆኑ የሙያ መስኮች ውስጥ የነርስ፣ መምህር፣ የምክር አገልግሎት፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሳይንስን በመሰሉ ዘርፎች ይሆናል።

 መንግሥት በዚህ ዓመት ለዩኒቨርሲቲዎች $18 ቢሊየን ድጎማ ያደርጋል።

  

                                                         

የቫይረስ ክትባት - ደቡብ አውስትራሊያ

 

አምስት መቶ የደቡብ አውስትራሊያ የጤና ሠራተኞች አሁን በጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ክትባት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ይረዳ እንደሁ ለመፈተሽ የሚካሄድ የክሊኒክ ሙከራ ላይ ሊሳተፉ ነው።  

 በአዘቦቱ ለሳምባ ነቀርሳና የፊኛ ካንሰር የሚሰጠው Bacille Calmette-Guerin ክትባት ከሌሎች ተላላፊዎች የሰውነት የመከላከል አቅምን በመገንባቱ ይሁንታን ያገኘ በመሆኑ፤ የደቡብ አውስትራሊያ መንግሥት $200,000 ለክሊኒክ ሙከራ ማካሄጃ መድቧል። የሙከራ ሂደቱ የሚያካሂደው በደቡብ አውስትራሊያ ጤናና የሕክምና ምርምር ተቋም ነው። 

 የደቡብ አውስትራሊያ ጤና ሚኒስትር ስቲፈን ዌድ ውጤቱ የጤና ሠራተኞችን የሰውነት የመከላከል አቅም ግንባታ በማዳበር የቫይረሱን የጥቃት ኃይል ሊያዳክም ቢችል መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል። 

 

 

ቫይረስ - ዓለም አቀፍ

በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 1.7 ሚሊየን አልፏል።

 በኮቪድ - 19 ሳቢያ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ የሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

 ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ ከዘጠና አምስት ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ - 19 ተጠቅተዋል፤ ከሰባት ሺህ በላይ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

 አውስትራሊያ ውስጥ ባለፉት ሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። 

 በመላው አውስትራሊያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሺህ ሶስት መቶ አልፏል።

 አምሳ ስድስት አውስትራሊያውያን ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ድንጋጌዎችን ጥሰው በተገኙ ሰዎች ላይ ከአንድ ሚሊየን ዶላርስ በላይ መቀጮ ተጥሏል። 

ኩዊንስላንድ 460, ኒው ሳውዝ ዌይልስ 295, እንዲሁም ቪክቶሪያ ከአንድ መቶ በላይ መቀጮዎችን ጥለዋል።

                                                          

ቫይረስ - ተመላሽ አውስትራሊያውያን

 

በኮቪድ - 19 ቀውስ ሳቢያ በመላው ዓለም በያሉበት ቀርተው የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ አውስትራሊያውያን ዛሬ እሑድ የአገራቸውን ምድር መልሰው ይረግጣሉ። 

 የግሬግ ሞርታይመር - አንታርክቲክ ክሩዝ መርከብ መንገደኞች የነበሩ ዘጠና ስድስት አውስትራሊያውያን በቻርተር አውሮፕላን ሜልበርን ይገባሉ። 

 መርከቢቱ ዩራጓይ ባሕር ጠረፍ ላይ ካለፈው ወር ጀምራ መልሕቋን ጥላ ነበር።

 ከፔሩ፣ ሕንድና ኔፓል ተመላሽ አውስትራሊያውያን ሜልበርን ወይም ሲድኒ ያርፋሉ።

 ለሁለት ሳምንታትም በለይቶ ማቆያ ይቆያሉ።

 ላለፉት ሁለት ሳምንታት በለይቶ ማቆያ የሰነበቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ አውስትራሊያውያን ዛሬ ወደ ቤታቸው ይገባሉ።

                                                         

ቫይረስ ምጣኔ ሃብት 

 

በዚህ ሳምንት የሥራ አኃዝ ይፋ ሲደረግ የሥራ አጥነት ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል። 

 ወቅታዊው የፌብሪዋሪ የሥራ አጥነት መጠን 5.1 ፐርሰንት ነው።

 ኮሮናቫይረስ ምጣኔ ሃብቱ ላይ ባሳደረው አሉታዊ ተጽዕኖ ምክንያት የወርኃ ማርች የሥራ አኃዝ ሐሙስ ኤፕሪል 16 ይፋ ሲሆን የሥራ አጥነት መጠኑ 5.4 ፐርሰንት ሊደርስ እንደሚችል ከወዲሁ ግምታቸውን የገለጡ የምጣኔ ሃብት ተጠባቢዎች አሉ። 

አልፈውም የሥራ አጥነት መጠኑ ከ2016 ወዲህ ከፍተኛ በሆነ መልኩ እስከ 5.9 ፐርሰንት ይደርሳል ብለው ግምታቸውን የገለጡም አሉ። 

 የዌስትፓክ ምጣኔ ሃብት ተጠባቢዎች በበኩላቸው የአውስትራሊያ ምጣኔ ሃብት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ድቅቀት ውስጥ እንደሚገባና በዓመቱ መጨረሻ አካባቢም እንደሚያንሰራራ ይናገራሉ።

ይሁንና የ2020 የምጣኔ ሃብት ዕድገት ካለፈው ዓመት ባነሰ አምስት ፐርሰንት ላይ እንደሚያርፍ ይጠበቃል።

                                                         

 

 


3 min read

Published

Updated

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now