በኮሮናቫይረስ የተጠቁት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ ሜሪላንድ ወደ ሚገኘው ዎልተር ሪድ ወታደራዊ የሕክምና ማዕከል በማሪን ዋን ሔሊኮፕተር ተወስደዋል።
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካይሊ ማክኢናኒ "በሐኪማቸውና በሕክምና ኤክስፐርቶች ምክረ ሃሳብ መሠረት ፕሬዚደንቱ ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ዎልተር ሪድ ከሚገኘው ፕሬዚደንታዊ ጽሕፈት ቤት ሆነው ይሠራሉ" በማለት ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ትራምፕ ወደ ሆስፒታል ከመሄዳቸው በፊት ቀርጸው ባስተላለፉት አጭር ቪዲዮ "ደህና ነኝ። የላቀ ድጋፋቸውን የቸሩኝን ሁሉ ላመሰግን እሻለሁ" ብለዋል።
የዲሞክራት ዕጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንና ዕጩ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ከነባለቤቶቻቸው አካሂደው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ማይክ ፔንስና ባለቤታቸውም እንዲሁ ምርመራ ተደርጎላቸው ከቫይረሱ ነጻ ሆነው ተገኝተዋል።
ምርምራ ካካሄዱ በፕሬዚደንቱ አካባቢ የነበሩ የቅርብ ረዳቶችና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ውስጥ እስካሁን ስድስቱ በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጧል።

