ከአቅም በላይ እየሆነ የመጣውን ስርጭት በትብብር መከላከል ካልተቻለ በሌሎች ወረዳዎችም ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
መስከረም 29 - 2013 በአፋርና አማራ ክልል አዋሳኝ በሆነው ጭፍራ አካባቢ መጠነ ሰፊ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል፡፡
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በአማራ ክልል ምሥራቃዊ ክፍል እና በአጎራባች ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ መጠነኛ ጉዳት ማስከተሉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ያለፈው ዓመት የበረሃ አንበጣ መንጋው እንቁላል በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ መፈልፈል በመጀመሩ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡
የአንበጣ መንጋው በከፍተኛ መጠን ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች መካከል በሰሜን ወሎ ዞን ያሉ ወረዳዎች ይገኙበታል፡፡
ከሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአንበጣ መንጋው መታየት መጀመሩን በተለይም ለአብመድ የገለፁት የሰሜን ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ተገኘ አባተ አርሶ አደሩ በዘመናዊ እና ባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ የበረሃ አንበጣ መንጋው ለመጀመሪያ ጊዜ በሐብሩ እና ራያ ቆቦ ወረዳዎች ቢከሰትም በቅርብ ጊዜ ጉባላፍቶ እና ቆቦ ከተማ አስተዳደር አካባቢዎችም መከሰቱንም አቶ ተገኘ ገልጠዋል፡፡
አርሶ አደሩ የአንበጣ መንጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመከላከል ሥራው ቢጠመድም ችግሩ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ነው ምክትል ኃላፊው የገለፁት፡፡ ‘‘ኅብረተሰቡ አንዱን መንጋ ተከላክሎ ሲጨርስ ሌላ መንጋ እየተከሰተ ጉዳት ያደርሳል’’ ያሉት አቶ ተገኘ ወደመጨረሻም ተስፋ መቁረጥ እና መዳከም መታየቱን፤ የአንበጣ መንጋውም እያየለ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
እስካሁን ባለው የበርሃ አንበጣ መንጋ ሥርጭት የሐብሩ፣ ራያ ቆቦ እና ጉባላፍቶ ወረዳዎች ድንበር አካባቢ ሰብል ማዳን አልተቻለም፡፡
የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደዘገበው የበርሃ አንበጣ መንጋው በአዲስ ወደዞኑ እየገባ መሆኑንም የገለፁት ምክትል መምሪያ ኃላፊው ‘‘ሀገራዊ ትብብር በማድረግ ችግሩን በአፋጣኝ መቆጣጠር ካልተቻለ አስከፊ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል’’ ብለዋል፡፡
በአካባቢው ለተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ የአየር ላይ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ቢሆንም ያለው አቅርቦት ከአንበጣ መንጋው ስርጭት አንፃር በቂ አለመሆኑን እና ተጨማሪ ኃይል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
የበረሃ አንበጣ በአማራ ፣ ትግራይ ፣ አፋር ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መከተሰቱን የግብርና ሚኒስቴር መግለፁ ይታወሳል።

