ትናንት በሸራተን አዲስ ሆቴል በተከናወነው የዲኤስቲቪ (መልቲቾይዝ) የሚዲያ ሾውኬዝ ተከናውኗል፡፡
የአፍሪካ ግዙፉ የስፖርትና መዝናኛ ይዘቶች አቅራቢ የሆነው መልቲቾይዝ በሚሰራባቸው የአፍሪካ አገራት ሁሉ ዓመታዊ የሚዲያ ሾውኬዝ እያከናወነ ሲሆን የመልቲቾይዝ ኢትዮጵያ ሚዲያ ሾውኬዝም ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በደማቅ ሁኔታ በሸራተን ተከናውኗል፡፡
የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ገሊላ ገ/ሚካኤል እንደገለፁት “የአፍሪካን ታሪክ በአፍሪካውያን” ብሎ የሚያምነው መልቲቾይዝ የአፍሪካን ገፅታና ታሪክ በአፍሪካዊ ባለሙያዎችና አፍሪካዊ አቅም ለዓለም እያስተዋወቀ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለአፍሪካዊ ባህልና እሴት ቅርብ የሆኑና የእኔነት ስሜት የሚፈጥሩ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ይዘቶች ለደንበኞቹ በማቅረብ ላይ ነው፡፡
እንደ ወ/ሮ ገሊላ ገለፃ ከሚያከናውናቸው የራሱ ኢንቨስትመንቶች በተጨማሪ በሚሰራባቸው አካባቢዎች ሁሉ የየአገራቱን ገፅታ፣ ባህል፣ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ለዓለም በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ የአህጉራችን አፍሪካ የዓለም ወካይ (ምልክት) ነው፡፡
በስፖርትና መዝናኛ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ጥራትና የዋጋ ተመጣጣኝነት ያላቸውን በብቸኝነት የአውሮፓ ፕሪሚየር ሊግን እንዲሁም፣ ቻምፒየንስ ሊግ፣ ኤፍ ኤ ካፕና ሌሎች የስፖርት ውድድሮችን ያቀርባል፤ አዳዲስና የቆዩ የሆሊውድ ፊልሞችን፣ ዶክመንተሪዎችን፣ ተከታታይ ፊልሞችን፣ የልጆች ይዘቶችን በተለያዩ የፓኬጅ አማራጮች ያቀርባልም ብለዋል፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ እንዳሉት መልቲቾይዝ አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ በሚያደርጉና በቴክኖሎጂ የዳበሩ፣ ከፍላጎቶቻቸው ጋር ተመጣጣኝ እሴት ያላቸውን የስፖርትና መዝናኛ ቻናሎችን ለተመልካቾች እያቀረበ ነው፡፡
በሾውኬዙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ኢድሪስ በበኩላቸው ዲኤስቲቪ የኢትዮጵያን የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነት፣ የፕሮዳክሽን አቅምና የገፅታ ግንባታ ላይ እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ የዲኤስቲቪ የስራ እንቅስቃሴን ያደነቁት አቶ መሀመድ አህጉር አቀፍ ተደራሽነት ያለውን እንደ ዲኤስቲቪ ያለ የይዘት አቅራቢ ለማገዝ መስሪያ ቤታችን ሁሌም ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በበኩላቸው ዲኤስቲቪ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እድገት በፋይናንስና በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እያበረከተ ካለው ጉልህ አስተዋፅ በተጨማሪ ኳሳችንን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን በመስጠት ተቀባይነቱንና ተደራሽነቱን የላቀ አድርጎልናል ብለዋል፡፡ ይህ ደግሞ የክለቦችንና የተጨዋቾችን፣ የአሰልጣኞችን፣ የዳኞችን ተወዳዳሪነት ጨምሯል፣ በእግር ኳሳችን የዲሲፕሊንና Fair Play ለውጥ መጥቷል፤ ተጨዋቾች፣ ዳኞችና አሰልጣኞች በአፍሪካ ደረጃ እንዲታዩ አቅማቸው እንዲታይና እንዲተዋወቁ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ብለዋል፡፡
በሾውኬዙ እንደተገለፀው ዲኤስቲቪ በየጊዜው በኤች.ዲ ጥራት የሚቀርቡ ቻነሎችን ቁጥር በማብዛት ላይ የሚገኝ ሲሆን ከዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ቻነሎች በተጨማሪ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰራጩ የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛዎችን (ቻናሎችን) በዲኤስቲቪ እንዲታዩ በማድረግ ደንበኞች ሁሉንም አይነት ሀገራዊ ዘገባዎች እንዲያገኙ እየተደረገ ነው፡፡

በቅርቡ የተለየ ትኩረት በመስጠት ለኢትዮጵያውያን ባህል፣ ገፅታና አህጉር አቀፍ ተደራሽነት የሚሰራ “አቦል” የተሰኘ የቴሌቪዥን ቻናል አቅርቧል፤
በ መልቲቾይዝ አካዳሚ “ታለንት ፋክተሪ” አማካኝነት የወደፊት የፊልም ጥበብ ባለሙያዎችን እያሰለጠነ ለአፍሪካ ፕሮዳክሽንና ይዘት ፈጠራ /Creativity/ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ወጣት ባለሙያዎችም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁሉም የአፍሪካ አካባቢ የየአገራቱን ገፅታና ታሪክ ከማስተዋወቅ ባለፈ ለኪነ ጥበብና ሚዲያ ባለሙያዎች፣ ለእግር ኳስ ተጨዋቾች፣ ዳኞችና አሰልጣኞችም በዓለም አቀፉ የስፖርትና መዝናኛ ኢንዱስትሪ ውስጥ ታላቅ የግንኙነት ዕድል እየፈጠረና እያስተዋወቀ ይገኛል ተብሏል፡፡
በሾውኬዙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የመልቲቾይስ ዲኤስቲቪ ደንበኞች ተገኝተዋል፡፡
ሾው ኬዙ በየዓመቱ እንደሚከናወን ከመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ዲፓርትመንት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]

