ግብፅ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ለማጥበቅ እየዳዳች ነው

***"በአሁኑ ወቅት አንድም ግብፃዊ ትግራይ ውስጥ የለም" የግብፅ ኤምባሲ በኢትዮጵያ

sawir muqdisho

View of Mogadishu. Source: SBS

በግብፅ የአፍሪካ ጉዳዮች የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ሸሪፍ ኢሳ የልዑካን ቡድን መሪነት ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ዘልቆ መመለሱን የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሥራ ጉብኝቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የልዑካን ቡድኑ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አብዲረዛቅ ጋር ተገናኝቶ "በሶማሊያ ልማቶች፣ በአጎራባች አገራት ቀጣናዊ ሁኔታዎችና በአፍሪካ ቀንድ ጸጥታና መረጋጋት ላይ ያሏቸውን ተፅዕኖዎች፣ እንዲሁም የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነቶች" ዙሪያ ተነጋግሯል።       

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሐመድ አብዲረዛቅም በበኩላቸው ከልዑካን ቡድኑ ጋር በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ላይ መነጋገራቸውን ጠቅሰው "ሶማሊያና ግብፅ ጠንካራ ወንድማዊ ወዳጅነትና ትስስሮሽን ይጋራሉ። ግንኙነታችንንም ይበልጡን ማጠናከር እንሻለን" ብለዋል። 

በሶማሊያና ግብፅ ግንኙነት የቅርብ ተመልካቾች ዘንድ የግብፅ ልዑካን ቡድን ወደ ሶማሊያ መላክ አንዱ አስባብ በቅርቡ ያለ ሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ዕውቅና የግብፅ የትምህርት ሚሽን ቡድን በፑንት ላንድ ጉዳይ ተመሳጥሯል በሚል ክስ ሶማሊያን ለቅቆ እንዲወጣ ማድረጉና የቱርክ ከሶማሊያ ጋር ወዳጅነቷን ማጠንከር ለግብፅ አሳስቢ መሆን ጋር ተዳምሮ እንደሆነ አመላክተዋል።

በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የግብፅ በአፍሪካ ጉዳይ ከፍ ያለ ፍላጎት ማሳየት ከኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ መሆኑም ተጠቅሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር ኦሳማ አብደል-ክሃሌም "በአሁኑ ወቅት አንድም ግብፃዊ ትግራይ ውስጥ የለም" ሲሉ ለአንድ የአረብ ድረ-ገጽ ዜና አውታር ትናንት ረቡዕ ዲሴምበር 16 2020 ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል በተፈጠረው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ምን ያህል ቁጥር ያላቸው ግብፃውያን ከመቀሌ እንደወጡ ባይገልጡም በተባበሩት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ትብብር ዜጎቻቸው መውጣት እንደቻሉ አስረድተዋል። 

በሌላ በኩል ግብፅ መቀሌ ውስጥ የ$10 ሚሊየን ሙዋዕለ ንዋይ ፍሰት እንዳላትና በተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያም ምናልባትም መቀሌ የሚገኙት የግብፃውያኑ ፋብሪካዎች ለኪሳራ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ በኢትዮጵያ የግብፃውያን ኢንዱስትሪያዊ ዞን ዋና ኃላፊና የግብፅ ሙዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች ፌዴሬሽን ምክትል ኃላፊ ኤላ ኢል-ሳቅቲ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።       

 

 


2 min read

Published

Updated

By Stringer Report


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now