የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደት ወቅት በአዲስ አበባ ሕግና ደንብን በመጣስ የተገኙ ሁለት የምርጫ አስፈፃሚዎች ከሥራ መሰናበታቸውን ገልጿል። ቦርዱ በተጨማሪም በአዲስ አበባና በተወሰኑ ክልሎች የድምፅ ቆጠራ አሁንም እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ማክሰኞ ዕለት ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት መግለጫ፣ በድምፅ መስጫ ቀንና ከዚያ በኋላ በተካሄዱ የክትትል ሥራዎች መሠረት በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የሕግ ጥሰቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ መገኘት የማይገባቸው ግለሰቦች በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች መታየታቸውን በተመለከተ የደረሱ ጥቆማዎችን ቦርዱ በክትትል ቡድኖቹ በማጣራት አንዳንዶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ማረጋገጡን ገልጿል። በዚህም መሠረት በሕግ ውጪ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ ሁለት የምርጫ አስፈጻሚዎች ከሥራ ተሰናብተዋል።
ሰብሳቢዋ እንዳሉት፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች ሲቪል የለበሱ የመንግሥት አስተዳደር አካላት ያለፈቃድ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች በመግባታቸው ከቦታው እንዲወጡ እርምጃ ተወስዷል።
በሌላ በኩል፣ በቡርጂ የምርጫ ጣቢያ "የምርጫ አስፈጻሚዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ራሳቸው ሲሞሉ ተገኝተዋል" በሚል የቀረበ ጥቆማ በመረጋገጡ፣ ጣቢያው እንዲዘጋና በስፍራው የተካሄደው ምርጫ እንዲሰረዝ መደረጉን ቦርዱ ገልጿል።
ቦርዱ በምርጫ ቀን የድምፅ መስጠት ሂደቱ በአብዛኛው በሰላምና በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን ቢገልጽም፣ በአዲስ አበባ በተፈጠሩ ረጃጅም ሰልፎች ምክንያት የድምፅ መስጫ ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6:00 ድረስ መራዘሙን አስታውቋል። ለመዘግየቱ ዋና ምክንያቶች መካከል በመራጮች መዝገብ ላይ ስም የመፈለግ ሂደት መርዘም፣ በአንዳንድ ጣቢያዎች የእጩዎች ቁጥር እስከ 123 መድረሱ እና መራጮች በምስጢር ድምፅ መስጫ ክፍል ውስጥ የሚወስዱት ጊዜ መርዘሙ ተጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ1,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ የድምፅ ቆጠራ ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ቦርዱ፣ በሲዳማ፣ በጋምቤላ፣ በአማራ እና በሶማሌ ክልሎችም በተወሰኑ ጣቢያዎች ቆጠራው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የፓርቲ ወኪሎችና ታዛቢዎች ወደ አንዳንድ ጣቢያዎች እንዳይገቡ የተደረገ እገዳ መኖሩን ቦርዱ አረጋግጦ፣ ችግሩ ተፈትቶ በቆጠራ ሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጿል።
በትናንትናው ዕለት የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ በአዲስ አበባና በሀዋሳ በአንዳንድ ጣቢያዎች የፓርቲ ወኪሎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መታየታቸውን፣ በሀዋሳ ቱላ ወረዳ አንዳንድ የቀበሌ አመራሮች በምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ መግባታቸውን፣ እንዲሁም ማኅተም ያልተደረገባቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች መሰራጨታቸውን እና ታዛቢዎች ወደ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ጨምሮ በርካታ ጉድለቶችን አመልክቷል።
ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚህ ዙሪያ ሲናገሩ፣ “እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት እና ታዛቢ ተቋም በመሬት ላይ ያገኙትን ሁኔታ በትክክል አቅርበዋል ብለን እናምናለን” ብለው፣ በሪፖርቱ የተጠቀሱ ጥቆማዎች በቦርዱ እየተጣሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የምርጫ ውጤት በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ከተጠናቀቀ በኋላ በየጣቢያዎቹ ለሕዝብ እየተለጠፈ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፣ ውጤቶቹ በምርጫ ክልልና በቦርዱ ዋና ማረጋገጫ ማዕከል ተጣርተው በሕግ በተደነገገው ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል።
ቦርዱ እንዳስታወቀው፣ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ይፋ የሚሆን ሲሆን፣ አስገዳጅ ቅሬታዎች ከቀረቡ ግን የመጨረሻ ውጤት እስከ 20 ቀናት ድረስ ሊራዘም ይችላል።

