የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ተቋም በ19ኛው ክፍለ ዘመን የዳግማዊ አፄ ተዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ የፀጉር ማስያዣን ተደራድሮ ከ150 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ለማድረግ ማስቻሉን አስታወቀ።
ተመላሽ የፀጉር ማስያዣው በ1868ቱ የመቅደላ ጦርነት ወቅት ከሌሎች በሺህዎች ከሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ቅርሳ ቅርሶች ጋር በእንግሊዝ ወታደሮች ተወስደው ከነበሩት መካከል አንዱ ነው።
የባለ አደራ ተቋሙ ድርድሩን የከወነው ከ Bertolami Fine Art ጋር ሲሆን፤ በተቋሙ በኩል ድርድሩ የተመራው የበጎ አድራጎት ድርጅቱ መሥራችና የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ኃይለሥላሴ ነው።
ከሮም ጨረታ ቀራቢነት ቀርቶ በሕዝብ ሃብትነት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ በመሰናዶ ላይ ያለው የእቴጌ ጥሩወርቅ የፀጉር ማስያዣ በ2026 መጀመሪያ ግድም ወደ ኢትዮጵያ በተሟላ ክብር እንደሚመለስ ይጠበቃል።
ልዑል ኤርሚያስ፤ Bertolami Fine Artን አክሎ፤ በድርድሩ ለተሳተፉና የችሮታ እጆቻቸውንም ለዘረጉ ወገኖችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በመሉ ከፍ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
"አመኔታ ላይ መሠረቱን በጣለ ትብብርና የጋርዮሽ መከባበር፤ ሁነኛ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ቅርሶች ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተደራሽ እንዲሆኑ፣ ዓለምም እንዲያጠናቸው፣ አድናቆቱንም እንዲቸራቸውና ትምህርትም እንዲቀስምባቸው ማስቻሉን እንቀጥልበታለን" ብለዋል።
ቀደም ሲልም በተመሳሳይ መልኩ በ2024 በየኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ተቋም አማካይነት የአፄ ቴዎድሮስ ጋሻ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ከስኬት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

His Imperial Highness Prince Ermias Sahle-Selassie Haile-Selassie and the Magdala Shield. Credit: RET
የባለ አደራ ተቋሙ ልግስናውን የቸረው በሃረኬይን ሜሊሳ ተጎድታ በማገገም ላይ ላለችው ጃማይካ የማንሠራሪያ ለማድረግ ነው።
የኢትዮጵያ ንጉሣዊ በጎ አድራጎት ባለ አደራ ተቋም ለጃማይካ ልገሳ ማድረጉ የተገለጠው፤ በጃማይካ የባሕል፣ ፆታ፣ መዝናኛና ስፖርት ሚኒስትር ኦሊቪያ ግራንጅ የካቢኔ ወቅታዊ ማብራሪያ ወቅት ነው።
ሚኒስትሯ፤ ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ ኃይለሥላሴ ለጃማይካ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሩ ሆልነስ በላኩት የማፅናኛ ደብዳቤ፤
"ጃማይካ በሃረኬይን ሜሊሳ ለደረሰባት ጉዳት ጥልቅ ሐዘኔን ለመግለፅ እሻለሁ። የጠፋው ሕይወትና ለጉዳት የተዳረገው የጃማይካ መሠረተ ልማት ሐዘንን ያሳድራል፤ ተግዳሮቶችንም ይደቅናል። እርስዎ በመልሶ ግንባታ ሂደት ጃማይካን ወደ ተሻለ ዕድል እንደሚመሩ አውቃለሁ" ማለታቸውን አንስተዋል።
አክለውም፤ በኢትዮጵያና ጃማይካ መካከል እስካሁን ፀንቶ የቆየውን ወዳጅነት ነቅሰው በምልሰት በማውሳትም በሚቻላቸው አቅም ሁሉ የግንባታ ሂደቱን እንደሚያግዙም ገልጠዋል።
ቃላቸውን ከግብር ጋር በማዋደድም አምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር ለጃማይካ የአደጋ ዝግጁነትና ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ቢሮ ስለ መቸራቸው በሚኒስትሯ ተመልክቷል።
Share

