”የእንጦጦ ፓርክ የተሻለ ነገን እንድናይ አድርጎናል” ሲሉ በፓርኩ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው እናቶች ተናግረዋል።
ሰባት ወራትን በፈጀ ጊዜ ተገንብቶ ትናንት በይፋ የተመረቀው የእንጦጦ ፓርክ ከመስህብነት ባሻገር በስራ እድል ፈጠራ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።
ፓርኩ በውስጡ ባቀፋቸው የኪነ ጥበብ፣ መዝናኛና ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ደግሞ እንጨት በመልቀም ሲተዳደሩ ለነበሩ ከ460 በላይ እናቶች የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል።
አዜአ በስፍራው በመገኘት ያነጋጋራቸው የስራ ዕድሉ ተጠቃሚ እናቶች እንዳሉት፤ በፓርኩ ውስጥ የተፈጠረላቸው ስራ ፈተና የሆነውን ህይወታቸውን ማሻሻል ችሏል። ”የእንጦጦ ፓርክ የተሻለ ነገን እንድንመለከት አድርጎናል” ሲሉም ገልጸዋል።
የሶስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አዛለች ሰመጉ ላላፉት 20 ዓመታት በእንጦጦ ጫካ ውስጥ እንጨት መልቀምን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎችን አሳልፈዋል።
አታካች የሆነውን የእንጨት ለቀማ ህይወት ለመሸሽ ልጆቻቸውን ትተው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አረብ አገር ተሰደው እንደነበርም ነው ለኢዜአ የገለጹት።
“ነገር ግን ያሰብኩት ሳይሳካ ከአምስት ወራት ቆይታ በኋላ በአእምሮ ጤና እክል ምክንያት ተመልሼ በድጋሚ እንጨት መልቀም ስራ ላይ ተሰማራሁ” ብለዋል።
በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የተፈጠረላቸው የስራ እድል ለቤተሰቦቻቻው የተሻለ ነገን እንደሚያመጣላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የዕድሉ ተጠቃሚ እናት ወይዘሮ ወርቅነሽ ዶያ ከእጅ ወደ አፍ በሆነው የእንጨት መልቀም ስራ ሁለት ልጆቻቸውን ለማሳደግ አቅም እንዳጠራቸው ገልጸዋል።
በአቅም ማነስ ምክንያት አንድ ልጃቸውን ለዘመድ እንደሰጡ ጠቅሰው፤ ሌላኛዋ ልጃቸውንም ቢሆን ከዘጠነኛ ክፍል በላይ ማስተማር እንዳልቻሉ ነው የሚናገሩት።
ጾማቸውን ያደሩበትን ቀኖች የሚያስታውሱት ወይዘሮ ወርቅነሽ በእንጦጦ ፓርክ የተፈጠረላቸው የስራ እድል ከገቢ ባሻገር የአእምሮ እረፍት እንደሰጣቸው ገልጸዋል።
“የተፈጠረልንን እድል በመጠቀም ነገን ከዛሬ ወደ ተሻለ ሁኔታ መቀየር አለብን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ በለጠች ማጃ ናቸው።
የእንጦጦ ፓርክ በግንባታ ሂደት ላይ አራት ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩ ተጠቁሟል።

