"ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገፍቶ የመግባት እንቅስቃሴዋን አባብሳለች" - የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

*** “ጦርነት አያስቸኩልም..." - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

Ambassador Dina Mufti

Ambassador Dina Mufti Source: Getty

ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገፍቶ የመግባት እንቅስቃሴዋን አባብሳለች ሲል የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሰሰ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንደተናገሩት ሱዳን በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ የምታደርገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያለውን ችግር ማጉላት ያልፈለገችው ጉዳዩን ቀጠናዊ ላለማድረግ እንደነበር ገልፀው የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ ውጥረት ላይ እንደደረሰ አንስተዋል።

"ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ ኃይሎች ጋር ጦርነት ብታደርግም ጦርነት ግን ትርፍ እንደሌለው ትረዳለች" ብለዋል አምባሳደር ዲና።  "ኢትዮጵያና ሱዳን ወደ ግጭት እንዲገቡ በማድረግ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የተለያዩ ሶስተኛ ወገኖች ፍላጎት እንዳለ" ገልፀው ኢትዮጵያ የጦርነት አማራጭ እንደማትጠቀም አክለዋል።

የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የጋራ ዕድገት እንጂ ጦርነት እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት። በአንፃሩ ሱዳን በድንበር አካባቢ አሁንም በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሠላምና ዲፕሎማሲ ቅድሚያ ትሰጣለች ያሉት ቃል አቀባዩ የሱዳን ጦር ወደ ድንበሯ ጥሶ በመግባት እያደረገ ያለውን ሕገወጥ እንቅሰቃሴ መታገሷ ግን "ከፍርሃትና ከመወላወል ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ" ገልፀዋል።

ድንበሩ እስኪካለል ድረስ ነባራዊው ሁኔታ ባለበት እንዲቆይ (ሁለቱም ሀገራት በነበሩበት እንዲቆዩ) እ.ኤ.አ በ 1972 ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ያነሱት ቃል አቀባዩ  የአሁኑ የሱዳን ድርጊት ይህን ስምምነት የሚጥስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አምባሳደር ዲና እንዳሉት ሱዳን ጦሯን አሰልፋ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግፋት የጀመረችው ፣ በድንበር አካባቢ የሳሳ የመከላከያና የጸጥታ ሁኔታ ስላለ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው ከጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ማለትም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ዘመቻ ከጀመረ ከ 6 ቀናት በኋላ ሱዳን በድንበር አካባቢ ጦሯን አሰልፋ ጥቃት መፈጸም መጀመሯ ተገልፆ ነበር።

በ1902እኤአ የተደረገውን የድንበር ማካለል ታሪክ ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ የጋራ የድንበር ማካለል ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች በመመለስ የሁለቱን አገራት የድንበር ችግር መፍታት ተገቢ እንደሆነም አስምረውበታል ቃል አቀባዩ።

በመግለጫው በጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱላቸው አምባሳደር ዲና "ኢትዮጵያ ጦርነት ትጀምራለች ወይ?" ለሚል ጥያቄ ኮምጨጭ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  እንዳሉት “ጦርነት አያስቸኩልም ፣ ይሁንና አፍንጫህን የመታህን ወዲያውኑ አፍንጫውን ላትመታው ትችላለህ ፤ ሌላ ጊዜ ግን አንገቱንም ልትቆርጠው ትችላለህ” ብለዋል።

ይሁን እንጅ አሉ አምባሳደር ዲና ፣ የበለጠ ትኩረታችን በዲፕሎማሲ ችግሩን ለመፍታት ነው። “ስለዲፕሎማሲ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ የሚያውቅ የለም” በማለት አሁንም ችግሩን በውይይት ለመፍታት ሱዳን ዝግጁ መሆን አለባት ብለዋል።

[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]

 

 


2 min read

Published

By Demeke Kebede


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now