የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ የገቢው መጨመር በዋናነት አገልግሎቶቹ በብዛት ጥቅም ላይ በመዋላቸውና በቴሌብር የሚተላለፈው ገንዘብ በመጨመሩ እንጂ፣ ባለፈው ታኅሳስ ወር በተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ አክለውም “ይህ ስኬት ኩባንያችን ወደ ዲጂታል አገልግሎት አቅራቢነት ለመሸጋገር የነደፈው የሶስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ውጤታማ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው” ብለዋል።
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ደንበኞች የተጠቀሙት የሞባይል ዳታ የ46.6 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ ለገቢው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ድርጅቱ በቅርቡ የተደረገው የሂሳብ ማሻሻያ ሳይካትት 35.62 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ታክስ መክፈሉንም አረጋግጧል።
ኩባንያው ከ88 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የገለፀ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ83 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል።
ይሁን እንጂ ዘንድሮ ለሚገነባቸው ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንደሚፈልግ ያስታወቀው ኩባንያው፣ ባንኮች የሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን የሚያሟላ እንዳልሆነ አልሸሸገም።
በዚህም ምክንያት አስፈላጊውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ አቅራቢዎች ጋር የብድር ድርድር እያደረገ መሆኑን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ አጠቃላይ የደንበኞቹ ቁጥር 87.1 ሚሊዮን መድረሱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8.2 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አስታውቋል።
ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ “በኢትዮጵያ የሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት 108 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የመሠረተ ልማት ሥራዎች ተከናውነዋል” ሲሉ ተቋሙ የወደፊት ፍላጎቶችን አስቀድሞ እያዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የድምፅ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር 84 ሚሊዮን እንደደረሰ የገለፁት ፍሬሕይወት ድርጅቱ አገልግሎት አጠቃቀምን በተመለከተ 13.3 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ማስተማሩንም ገልፀዋል።

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 278 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፤ ከእነዚህም ውስጥ 130 ያህሉ የገጠር አካባቢዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም አጠቃላይ የጣቢያዎች ቁጥርን 10 ሺህ 288 በማድረስ የዕቅዱን 98.5 በመቶ ማሳካት ተችሏል። ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት “በተለይ የገጠር ሳይቶችን ቁጥር በመጨመር ከዚህ ቀደም አገልግሎት ተደራሽ ባልነበረባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚው እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል” ብለዋል።
በሌላ መልኩ133 አዳዲስ ከተሞች የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውንና ሽፋኑም 74 በመቶ መድረሱን ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልፀዋል። ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም “በአጠቃላይ የ4G አገልግሎት ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥር 1 ሺህ 069 ደርሷል” ብለዋል።
ተቋሙ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ወደ 204 ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 81 የሚሆኑት በስድስት ወሩ ለአገልግሎት የበቁ አዳዲስ የምርት ዓይነቶች መሆናቸውን ድርጅቱ በሪፖርቱ አመልክቷል።
የቴሌብር አገልግሎት የደንበኞች ቁጥር 58.61 ሚሊዮን መድረሱን ያብራሩት ሥራ አስፈፃሚዋ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 1.94 ትሪሊዮን ብር ዝውውር ተደርጎበታል።
ተቋሙ ‘ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ 6.88 ትሪሊዮን ብር በቴሌብር ተዘዋውሯል ብለዋል። ከተለያዩ ባንኮች ጋር በአጋርነት በመሥራት ላይ የሚገኘው ቴሌብር፣ በፋይናንስ ተደራሽነት ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ መሆኑ ተጠቁሟል።
በዚህም 16.19 ሚሊዮን ደንበኞች የብድር አገልግሎት ማግኘት የቻለ ሲሆን፣ 34.41 ቢሊዮን ብር የሚሆን ገንዘብ ደግሞ በደንበኞች መቆጠቡ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ድርጅቱ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባን በማከናወን 22 ሚሊዮን ዜጎችን መመዝገቡን ገልፀዋል። የኢትዮ ቴሌኮም ምዝገባ እንደ ሀገር ከተከናወነው ጠቅላላ ምዝገባ ውስጥ የ69 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከ383 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የገለፁት ፍሬሕይወት ድጋፉ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለሰብዓዊ ዕርዳታ መዋሉን ማዋሉንም አክለው ገልፀዋል።

