ጤና ሚኒስቴር እንደገለፀው ዛሬ መጋቢት 30፣2013 ዓ ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያ ዩኒየን አባቶች እና መሪዎች የኮቪድ 19 ክትባት ወስደዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹም ህብረተሰቡ አሁን ላይ ደረጃ በደረጃ እየተሠጠ ባለው የክትባት አገልግሎት ሳይዘናጋ የኮቪድ 19 መከላከያ መንገዶችን ማለትም የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛን ማድረግ፣ ርቀትን መጠበቅ ተጠናክሮ መተግበር እንዳለበትም ጭምር አሳስበዋል ብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የብጹዕ ወቅዱስ ፖትሪያርክ ልዩ ጽ/ቤትና የዉጪ ጉዳይ መምሪያ የበላይ ኋላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ቡጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዉያን፣ በሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያ ዩኒየን ፕሬዝዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛ የኮቪድ 19 ክትባት ተከትበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንዳለው ክትባቱን የወሰዱ የኃይማኖት አባቶች መላው ህብረተሰብም በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚነሱ የሀሰት መረጃዎች ምክንያት ሳይዘናጋ የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመግታት የሚወሰዱ የመከላከያ እርምጃዎችን በተሟላ መልኩ መተግበርና አሁን ላይ እየተሰጠ ያለውን የክትባት አገልግሎትም በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ማስተላለፋቸውን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ እየተሰጠ ባለው የኮቪድ 19 ክትባት ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ የጤና ባለሙያዎች እየተከተቡ መሆኑን የገለፀው ጤና ሚኒስቴር ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ከ55-64 ዓመት ሆነው የሚታወቅ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም የኮቪድ 19 ክትባትን እየተሰጠ ይገኛል ብሏል፡፡
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]

