የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫቸውን ለአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ሰጥተዋል፡፡
በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይም በተመድ ሰራተኞች እስራት፣ በኦባሳንጆ የሰላም ድርድር ሂደት፣ በአዲስ አበባ ያሉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ከአዲስ አበባ የመውጣት እንቅስቃሴ እና የአሜሪካ ጫና ዙሪያ በርካታ ጥያቄዎች ተነስተውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ተመድ ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ 16 ሰራተኞቹና በሰመራ ደግሞ የእርዳታ መኪና ሾፌሮች በ”ብሔር እየተመረጡ” መታሰራቸውን መግለጹን አስመልክቶ የመንግስታቸው ምላሽ ምን እንደሆነ ለተነሳላቸው ጥያቄ “ የማንኛውም ተቋም ሰራተኞች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህጉ መሰረት መንቀሳቀስና ለህጉ መገዛት ይገባቸዋል፡፡ ለሽብርተኛው ድርጅት በማንኛውም መልኩ ድጋፍ ማድረግና ተያያዥ ነገሮች ለአገር ሉዓላዊነት ሲባል ተከልክለዋል፡፡ ስለሆነም በህግ ቁጥጥር ስር የመዋላቸው ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የሚቆጣጠረውና የሚመለከተው አካል ስላለ በትክክል የመታሰራቸውን ምክንያት ያ አካል ነው የሚያውቀው” ብለዋል፡፡
ይሁንና አሉ አምባሳደር ዲና በማብራሪያቸው “ይሁንና የተመድ ሆነ የማንም ተቀጣሪ መሆን ከተጠያቂነት አያድንም። የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የታወጀ አዋጅ ነው፡፡ ስለሆነም ተጠያቂነት ፆታ ፣ ዘር፣ ኃይማኖትና ስራ ጭምር አይለይም። ተመድ በመሆኑ ከህግ በላይ አይሆንም” ሲሉ አክለዋል፡፡
በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛውና የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ መቀሌ ሄደው ከሕወሃት አመራሮች ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልና ሌሎችም፣ በአዲስ አበባ ደግሞ ከፕሬዝደንት ሳሕለወርቅ ዘውዴና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እንዲሁም ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመሄድ “ድርድር” ለማድረግ የሚያደርጉትን ጥረት በተመለከተ ለቃል አቀባዩ ጥያቄ ተነስቶላቸዋል፤ ጋዜጠኞች “የኦባሳንጆ እንቅስቃሴ ለማደራደር ነወይ፤ መንግስት ከዚህ በፊት ከሽብርተኛ ጋር አልደራደርም ሲል ነበር፤ አሁንስ ለመደራደር አቅዷል?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡
አምባሳደር ዲና “ኦባሳንጆ የአፍሪካ ሕብረት ልዑክ ናቸው። የአፍሪካ ሕብረት መስራችና መቀመጫ በመሆናችን በሕብረቱ የሚደረጉ ጥረቶችን እናከብራለን፣ የአፍሪካዊ መፍትሄ አቀንቃኞች ነን። ይሁንና ከህወኃት ጋር ለመነጋገር በቅድሚያ ጥቃቱን ማቆም፣ የወረራቸውን አካባቢዎች መልቀቅ፣ እና የዚህን መንግስት ህጋዊነት መቀበል ይገባል፤ ይህ ለሠላም ሂደቱ መነሻ ይሆናል።” ሲሉ እምብዛም ያልተብራራ መልስ ሰጥተዋል፡፡
ሕወሓት በኩል ከአባሳንጆ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን ከቀናት በፊት ገልጧል።
ሌላው የአምባሳደሩ ማብራሪያ ያተኮረው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ኤምባሲዎች በተለይም የአሜሪካ ኤምባሲ፣ እንግሊዝና ሌሎችም ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ በአስቸኳይ እንዲወጡ መወትወታቸውን የተመለከተው ነበር፡፡ የኤስ.ቢ.ኤስ ዘጋቢ እንዳስተዋለው ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከ15 ያላነሱ ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ያስተዋለ ሲሆን አፍሪካዊቷ ዛምቢያ ደግሞ ቀዳሚዋ የኤምበሲ ሰራተኞቿን ከኢትዮጵያ ያስወጣች አፍሪካዊ አገር ሆናለች፡፡
ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና “ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የምዕራቡ ዓለም ሚዲያ የተዛቡ ዘገባዎች በርካቶችን አስደንግጧል” ያሉ ሲሆን “አዲስ አበባ ተከቧል፣ ኬንያ ድንበሯን ዘግታለች፣ መከላከያ ፈርሷል።” የሚል የሀሰት ዘገባ በማሰራጨት የኢትዮጵያን ትክክለኛ ሁኔታ አዛብተዋል ብለዋል፡፡ “እውነታው ግን አዲስ አበባና አካባቢው ሰላም ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
አምባሳደሩ የዲፕሎማቲክ ማሕበረሰቡ ከአዲስ አበባ ለመውጣት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ምክንያቱ ሁለት አይነት ነው ያሉ ሲሆን አንደኛው “ሆን ተብሎ የሚደረግና ሕዝቡን ለመረበሽ ታሳቢ ያደረገ ነው። መከላከያውን ለመከፋፈል ሆን ተብሎ ከጁንታውና ከሚዲያ ጋር በመቀናጀት የተፈጸመና ሕዝቡን ተስፋ ለማስቆረጥ የተደረገ ነው” ሲሉ ከስሰዋል፡፡
በአምባሳደሩ ማብራሪያ ሁለተኛው ደግሞ ባለማወቅ የተደረገ ነው፡፡ “አንዳንዱ ኤምባሲ ባለማወቅ ያደረገው ነው። ለእንደዚህ ያሉ ኤምባሲዎች ሰራተኞችና ዲፕሎማቶች እውነታውን በተለያዩ መድረኮችና ፕላትፎርሞች ለማስረዳት ጥረት እያደረግን ነው። ብዙዎቹም እውነቱን ተረድተዋል” ብለዋል፡፡
ስለአሜሪካ ጫናም ምላሽ ሰጥተዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፡፡ እሳቸው እንዳሉት “አሜሪካ የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜት ልታከብር ይገባል። ሕዝብ በየከተማውና ክልሉ ቁጣውን ገልጿል። የአራት ኪሎ መንግስት አቋም ብቻ የሚመስላቸውን ሁሉ ሕዝቡ በራሱ ፈቃድ ሰልፍ ወጥቶ እያሳየ ነው። በአሜሪካና በሌሎች አቋም ተቆጥቷል” ብለዋል፡፡
በተለያየ መልኩ የሚገለጸው የአሜሪካ ጫና በተለይም ከመጪው ጥር ጀምሮ ከአጎዋ ኢትዮጵያን ለማስወጣት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጧ ልክ አይደለም ብለዋል፡፡ እንደ አምባሳደሩ ገለፃ “ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ መወሰኗ አሜሪካ ትልቁን ስዕል ባለመረዳት ያደረገችው ነው። በአጎዋ ምክንያት የሚታለል የለም ፣ ሁሉም ነገር ከነጻነት በታች ነው” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ወደ ትግራይ ለሰብአዊ እርዳታ የገቡ መኪኖች 1 ሺህ 1 መቶ አርባ ሁለት ሲሆኑ የተመለሱት ግን ሁለት መቶ አርባ ሁለት ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
[ ደመቀ ከበደ - አዲስ አበባ]

